አዲስ አበባ፡- በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ልማት ፓርክ ስራ ከጀመሩ ባለሀብቶች መካከል በጨርቃጨርቅ ስራ ላይ የተሰማራው ሸንትስ ኩባንያ ለሰራተኞቹ የመኖሪያ ቤት እየገነባ እንደሆነ ተነግሯል።
የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ትንሳኤ ይማም በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ልማት ፓርክ የሚገኙ ኩባንያዎች ለሰራተኞቻቸው የምግብ እና የትራንስፖርት አገልግሎት ከማቅረብ ባለፈ መኖሪያ ቤት በመገንባት የሰው ሀይላቸውን በአግባቡ መያዝ እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ልማት ፓርክ ውስጥ ከሚገኙት ኩባንያዎች መካከል ለሰራተኞቹ የመኖሪያ ቤት በመገንባት ቀዳሚ የሆነው ሸንትስ የጨርቃጨርቅ ኩባንያ ሲሆን፤ ኩባንያው በቅጥር ግቢው ውስጥ ለ9000 ሰራተኞች የመኖሪያ ቤት እየገነባ ይገኛል። የተጀመረው ግንባታ ባለ አራት ፎቅ የሆኑ የአስር ህንፃዎች ስራ ሲሆን፤ በአሁን ወቅት የሁለቱ ህንፃዎች ግንባታ ተጠናቅቋል።
አሁን ላይ ከ4,500 በላይ ሰራተኞች ያሉት ይህ ድርጅት፤ በስራ አፈፃፀማቸው ጠንካራ እና ጥሩ ተሞክሮ ላላቸው ሰራተኞች ቅድሚያ በመስጠት በተጠናቀቁት ህንፃዎች ውስጥ 1,200 ሰራተኞች ያለምንም ክፍያ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ሆነዋል። በቀጣይም የህንፃዎቹ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ እያንዳንዱን ሰራተኛ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አቶ ትንሳኤ ገልፀዋል።
ድርጅቱ ለሰራተኞች የተለያዩ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ የገለፁት አቶ ትንሳኤ፤ በተለይም ከፆታዊ ግንኙነት ጋር በተያያዘ የሚመጡ በሽታዎችን መከላከል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም የአቻ ላቻ ስልጠናን ከመስጠት ጀምሮ የወረርሽኝ በሽታ በከተማው ሲከሰትም ሆነ ሲሰማ ቅድመ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርጉ ከወረዳው ጤና ጣቢያ ጋር በመሆን ስልጠና ይሰጣልም ብለዋል።
አያይዘውም፤ እንዲህ አይነቱ ተግባር የሰራተኞችን ጤና ከመጠበቅ ባለፈ የስራ ፍልሰትን የሚቀንስ፣ ተነሳሽነትን የሚጨምርና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ በጎ ተግባር መሆኑን በመግለፅ፤ ሌሎች ካምፓኒዎችም የሸንትስ ጨርቃጨርቅ ካምፓኒን ተሞክሮ በመውሰድ ለሰራተኞች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ለዚህም የተለያዩ የማማከር ስራዎችን በመስራት ኩባንያዎች ለሰራተኞች የመኖሪያ ቤት እንዲገነቡ ስምምነት ላይ ከመድረስም ባለፈ ለግንባታ የሚሆን ቦታ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2012
ፍሬህይወት አወቀ