ወይዘሮ መንበረ መቀጫ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 የሚገኘው “ሀበሻ የሽክላ ስራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር” ሰብሳቢ ናቸው። ማህበሩ በ11 አባላት በ2003 ዓ.ም ስራ መጀመሩን ይገልጻሉ። በአሁኑ ሰዓት ስራ የሌላቸው 23 እማወራዎች በመመልመል፤ አሰልጥኖ ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ የስራ እድል በመፍጠር የአባላቱን ቁጥርም 34 አድርሷል።
ማህበሩ እንስራና ጀበና በማምረትና በመሸጥ ስራ ላይ የተሰማራ ሲሆን፤ ምርቶቹን ለገበያ የሚያቀርበው በአንድ የመሸጫ ቦታ በመሆኑ ሰፊ የገበያ እድል ማግኘት እና ትርፋማ መሆን አልቻለም። አሁን ላይ ካፒታላቸው 10 ሺህ ብር ቢደርስም ዘመናዊ ማቃጠያ ምድጃ ስለሌላቸው የሚያገኙትን አብዛኛው ገቢ በየጊዜው በእሳት ለሚጎዳው ኩሽና ቆርቆሮ ስራ ወጪ እንደሚያውሉት ወይዘሮ መንበረ ይናገራሉ።
እንደ ወይዘሮ መንበረ ማብራሪያ፤ አምና የተለያዩ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ተሳትፈው የነበረ ቢሆንም በዘንድሮ ዓመት ጥር ወር ላይ በ ባህልና ቱሪዝም በኩል ተሳትፈዋል። ኤግዚቢሽን ማሳተፋቸው ወጪ አውጥተው፤ ጊዜያቸውን አቃጥለው ከመመለስ በስተቀር ምንም አይነት ገበያ እንዳላስገኘላቸው በመጥቀስ ለዚህ በምክንያትነት የሚያነሱት ምርቶቹን ከገበያ ጋር የሚገናኙበት ወቅት ላይ የገበያ ትስስር ያልተፈጠረ መሆኑን ያስረዳሉ።
ለምርት የሚያገለግሉ ጥሬ እቃዎች ከነጋዴዎች የሚረከቡ በመሆናቸው ውድ ከመሆኑም በላይ ከነጋዴ የሚያገኟቸው እቃዎች በየጊዜው እጥረት ስለሚያጋጥማቸው መቸገራቸውንና በስራቸው ላይም ለውጥና እድገት እንዳያመጡ እንቅፋት እንደሆነባቸው ይገልጻሉ።
በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በ2011 ዓ.ም ተደራጅተው የቆዳና የቆዳ ውጤቶች በማምረትና በመሸጥ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ሀብታሙ ተካ ጫማና ቦርሳ በማምረትና በመሸጥ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ይናገራሉ። ለሦስት ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን በመጠቆም፤ ካፒታላቸው 150 ሺህ ብር ቢሆንም ለምርቶቻቸው ጥሬ እቃ በሚፈልጉት ልክ በውድ ከነጋዴዎች ላይ ይገዛሉ። ትልቁ የስራቸው እንቅፍት ግን በቂ የገበያ ትስስር ያለማግኘታቸውና በዚህም ምክንያት በሙሉ አቅማቸው ያለመስራታቸው ነው።
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 የኮሪያ ዘማቾችና የዘማች ቤተሰቦች የሽመናና የስጋጃ ምንጣፍ ስራ የህብረት ስራ ማህበር ተወካይ ወይዘሮ ትዕግስት ባዩ እንደሚሉት፤ ማህበሩ ቀድሞም የነበረ ቢሆንም፤ በ1996 ዓ.ም ተጠናክሮ በሽመና፣ በስጋጃና በሹራብ ማምረት ስራ ላይ የተደራጀ ነው። የማህበሩ መስራች አባላት 16 ሲሆኑ ሙያ የሌላቸውን ሌሎች አስር አባላት መልምሎ በማሰልጠን የአባላቱን ቁጥር 26 አድርሷል። ከዚህም ሌላ ለሰባት ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩንም ይናገራሉ። በ50 ሺህ ብር መነሻ ስራ የጀመረው ይህ ማህበር አሁን ላይ ካፒታሉ 100 ሺህ ብር ደርሷል። የማህበሩ ዋነኛ ችግርም የጥሬ እቃ አቅርቦት እንደሆነና ከነጋዴ በጣም በውድ ዋጋ እንደሚገዙት ይናገራሉ።
እንደ ወይዘሮ ትዕግስት ባዩ ማብራሪያ፤ የበግ ጸጉር ከደብረ ብርሃን የሚያስመጡ ሲሆን፤ድርና ማጉን ከዚህ ቀደም እድገት ድርና ማግ ከሚል ድርጅት በተመጣጣኝ ዋጋ ያገኙ ነበር። በዘንድሮ አመት ግን ድርጅቱ ስራውን በማቆሙ መቸገራቸውን ይገልጻሉ። አያይዘውም፤ የህብረት ስራ ማህበራት መርሆአቸው ገበያው በማረጋጋትና ህዝብን በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ ማድረግ እንደመሆኑ መጠን በአነስተኛ ዋጋ ምርቶችን እያቀረቡ መሆኑን አብራርተዋል። ይሁን እንጂ፤ ለስራቸው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በሙሉ ከነጋዴ ስለሚገዙ ያለትርፍ እንደሚሰሩና ውጤታማ አለመሆናቸው ይጠቅሳሉ። በመሆኑም፤ መንግሥት ጥሬ እቃ በተመጣጠነ ዋጋ የሚያገኙበትን ሁኔታ ቢመቻችላቸው እነሱም ተጠቅመው ህብረተሰቡንም በመጥቀም በዘርፉ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ይናገራሉ።
የገበያ ትስስርን በተመለከተ በዘንድሮው ዓመት የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ባዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ ብቻ መሳተፋቸው ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ካልሆነ በስተቀር ምንም አይነት ሽያጭ አለመፈጸማቸው ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት ምርቶቻቸውን በማምረቻ ቦታቸው፣ በየቤተክርስቲያኑና በጎዳና ላይ ለመሸጥ እየተጣጣሩ መሆኑን ወይዘሮ ትዕግስት ይገልጻሉ።
እንደ ወይዘሮ ትዕግስት ማብራሪያ፤ በስራ ላይ ከሃያ አመታት በላይ የቆዩ ሲሆን ስራዎች የሚሰሩት በነበራቸው እውቀትና መሳሪያዎች በመሆኑ የእደጥበብ ሥራቸውን ለማሳደግ አዳግቷቸዋል። በጥበብ እየመሩት ላለመተው እየተፍጨረጨሩ መሆኑን በመጠቆም፤ ዘመኑ ከደረሰበት አሰራርና እድገት ላይ እንዲደርሱ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት ይጠይቃሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2012
ወርቅነሽ ደምሰው