አዲስ አበባ፤- በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲና በኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በጋራ የኢትዮ-ካናዳ የቢዝነስ ፎረም ሲካሄድ እንደተገለጸው÷ በኢትዮጵያና በአካባቢዋ በሚገኙ አገራት ያለው ከፍተኛ ገበያ የካናዳ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ በተለያየ ዘርፍ እንዲሳተፉ እንደሚያደርጋቸው ተገለጸ።
በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲ ከፍተኛ የንግድ ኮሚሸነር ሚስተር ሉዊ ላካስ እንደገለጹት÷ በኢትዮጵያና በአካባቢዋ ከፍተኛ የገበያ ዕድል አለ። ይህ ገበያ የካናዳም ሆነ የሌሎች ሀገሮች ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚስብ ነው። የካናዳ ኢንቨስተሮችም በኢትዮጵያ ያለው ገበያ ስቧቸዋል።
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትርና ሌሎች ከፍ ተኛ ባለስልጣናት የንግድ ማህበረሰቡን ወደ ኢትዮጵያ ይዘው የመጡት በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለመመልከትና ስምምነት በማድረግ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
“ከአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ምርጫችን በማድረግ በኢትዮጵያና በአካባቢዋ ያለውን ገበያ መጠቀም እንፈልጋለን ያሉት ሚስተር ሉዊ ላካስ በኢትዮጵያ ያለው ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ መንግስት እያካሄደ ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ እንዲሁም በቀጣይ የሚካሄደው ምርጫ አገሪቱን ጠንካራ የሚያደርግና ለኢንቨስተሮችም ምቹ በመሆኑ የካናዳ ባለሃብቶች ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚፈጥሩት ግንኙነት ትልቅ ውጤት የሚያመጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
የካናዳ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በማዕድን፣ በትራንስፖርት፣ በሆቴል፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖ ሎጂ፣ በገበያ፣ በኢንዱስትሪና በሌሎች ዘርፎች የመ ሰማራት ፍላጎት አላቸው። የካናዳ ኢንቨስተሮች በአፍሪካ ኢንቨስት ሲያደርጉ አዲስ ልምድ በመሆኑ ችግሮች ቢኖሩም ችግሮቹ አንድ በአንድ በመፍታት ውጤታማ እንሆናለን። ኢንቨስተሮቹም በቀጣይ ዓመታት እየበዙ እንደሚሄዱ እምነታቸው መሆኑን የንግድ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ስላለው ነባራዊ ሁኔታና በቀጣይ መንግስት ለመከተል ስላቀደው አገር በቀል የኢኮኖሚ እቅድ ለባለሃብቶቹ ከፕላን ኮሚሽን ማብራሪያ የሰጡት ዶክተር ሰዒድ ኑሩ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በሁለት አሐዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ብታስመዘግብም የገቢና ወጭ ንግድ አለመጣጣም፣ የተቋማት የማስፈጸም አቅምና ሙስና የኢኮኖሚው ቀጣይ ዕድገት ላይ ቀጣይ መሆን አለመቻሉም አመላክተዋል።
መንግስትም አገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይ ለማድረግ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አድርጓል። በማሻሻያው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ፣ ማይክሮ ኢኮኖሚክ ማሻሻያና ተቋማዊ የአሰራር ማሻሻያ አድርጓል። የቴሌኮም፣ የአየር መንገድ፣ በኃይልና በሌሎች ዘርፎችም የግሉ ዘርፍ እንዲገባ መንግስት እየሰራ መሆኑና ለግል አልሚዎች ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል። በግል የመንግስት አጋርነት ዘርፍም የግል ኢንቨስተሮች እንዲሳተፉ ለማድረግም የተለያዩ ጥናቶች እየተካሄዱና ለጨረታም እየወጡ መሆኑም ተገልጿል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ እና ልዑካን ቡድናቸውን ትናንት ማለዳ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ካናዳ በአያሌ መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ እንደ ሆነች ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሚካሄዱትን ለውጦች እና ሪፎርሞች እንደሚያደንቁና እንደ ወዳጅ፣ ደግሞም እንደ አጋር በጎን ሆነው ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም አውስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም በዲሞክራታይዜሽን እና ሁለተናዊ ብልጽግናን በመገንባት ላይ ስለተመሠረቱት ባለብዙ ገጽታ ቀጣይ የሪፎርም ሥራዎች ገልጸዋል።
ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የጋራ ፍላጎት በሚስተዋልባቸው የልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ንግድ፣ የኢነርጂ ኢንቨስትመንት፣ አግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ መድኃኒት እና ተያያዥ ግብአቶች ላይ በጋራ ስለመሥራት ተወያይተዋል። የቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ በጋራ መሥራትንም አንዱ የትብብር አቅጣጫ አድርገው አንስተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ