በጌዲዮ ዞን እና በአዋሳኙ የኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ተከስቶ በነበረው አለመግባባት ግጭቶች ተከስተው እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህ አለመግባባት ውስጥ በርካቶች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፤ ብዙዎች ለህልፈተ ህይወት እና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፤ ሀብት ንብረታቸውንም አጥተዋል።
ይህ ጥቁር ጊዜ ህዝቦችንም ሆነ አገሪቷን ዋጋ አስከፍሎ ሃዘን ላይ ጥሎም ነበር። መጨረሻው ግን በቂም በቀል፤ ነገን በክፋት በመጠበቅ አልተጠናቀቀም። ይልቁኑ በእውነተኛ እርቅና ፍቅር ነበር የተደመደመው። በተለይ እርስ በእርስ በሚያስተሳስር ባህል፣ ወግ፣ ሃይማኖት ባለው ማህበረሰብ መካከል ይህ ግጭት ቀድሞውኑ ቦታ አልነበረውም። በእውነት ላይ የተመሰረተው ግጭትን የማስወገድ ሂደት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ተፈጠረ?
አቶ አበበ ቢራራ እርቁን በሽምግልና ያስፈፀሙት የሽማግሌዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በአገሪቱ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል። ሆኖም ግን ችግሮችን ከመፍታት አንፃር በተሻለ መንገድ እውነተኛ ሰላም እና እርቅ መፈፀም የቻሉት እነርሱ መሆናቸውን ይናገራሉ። ምክንያቱ ደግሞ ሰላሙን ለማምጣት የኦሮሚያ እና ጌዲዮ ማህበረሰብ በሙሉ ፍላጎት መተባበሩን እንደ ምክንያት ያነሳሉ።
‹‹ሀብት ንብረት ወድሞ የሰው ህይወት የጠፋበት ግጭት ቢፈጠርም ህዝቡ ግን ለእውነተኛ ሰላም እና እርቅ ዝግጁ ስለነበር ስኬታማ መሆን ችለናል›› የሚሉት የኮሚቴው ሰብሳቢ፤ እያንዳንዱ ተጎጂ ቤት በመሄድ እና በማነጋገር ፤ በዳይና ተበዳይን ይቅር እንዲባባሉ ተደርጓል በማለት ገልፀዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ይቅር ባዩም ሆነ ይቅርታውን ተቀባዩ ሁለቱም ወገኖች ሊመሰገኑ እንደሚገባ ይናገራሉ።
አቶ አበበ በእርቅና ሰላም የማውረድ ሂደቱ ላይ በግጭቱ ወቅት ማረሚያ ቤት የገቡትም ተሳታፊ መሆናቸውን ይናገራሉ። ሁሉም ወገኖች ለግጭቱ ተጠያቂ መሆናቸውን በማመናቸውና እውነተኛ ሰላም አውርደው ፊርማቸውን በማኖራቸው የጠቅላይ አቃቤ ህግ እርቁን መቀበሉን ተናግረዋል። የማህበረሰቡ፣ የአስታራቂ ሽማግሌ ዎች እና የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ በዚህ እርቅ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል የሚል መልዕክት አስተላ ልፈዋል።
አቶ ገዙ አሰፋ የጌዲዮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ናቸው። ማህበረሰቡ የደራሮ ባህላዊ የዘመን መለወጫ ስነ ስርዓት ባከበረበት ወቅት እርቁን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ያለፉት ዓመታት በተለይም 2011 ዓ.ም ዞኑ ከባድ ችግር ውስጥ ወድቆ እንደነበር አንስተዋል። ሆኖም በዞኑ ያለው ማህበረሰብ ባደረገው እርብርብ ችግሩን ለመፍታት መቻሉንም ይናገራሉ።
አስተዳዳሪው በተለይ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጥሮ የነበረውን ልዩነት ለማጥበብ በአካባቢው ባህል እና ሽምግልና ስርዓት ችግሩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቀረፍ ጥረት መደረጉን ይናገራሉ። በተለይ በህዝቦች መካከል መቀራረብ፣አንድነት እንዲፈጠር በጌዲዮ አባ ገዳ የሚመሩ 48 የአካባቢው ሽማግሌዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱም አስረድተዋል። በዚህ መነሻም የታሰሩት ተፈትተው፤የተጣሉት ታርቀው፤ ልዩነት ጠፍቶና ይቅርታ ሰፍኖ በ2012 ዓ.ም የደራሮ በዓል ማክበር መቻሉን ተናግረዋል።
የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው፣ በዚሁ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ በመገኘት የወረዳውን ሰላምና የተፈፀመውን እርቅ እንዲሳካ ላደረጉ ሽማግሌዎችና መላው ማህበረሰብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
‹‹የተፈጠረውን ችግር አኩሪ በሆነው ባህላዊ ስርዓታችሁ በመፍታታችሁና አካባቢውን ወደ ቀደመው ሰላምና ልማት መመለስ በመቻላችሁ ልትመሰገኑ ይገባል›› ብለዋል። አሁንም ግን እኩይ ተግባር በሚፈፅሙ ቡድኖች ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን በርካታ ሴራዎች የሚጠነሰስበት፤ ብሄርን ከብሄር ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት ጥረት የሚደረግበት በመሆኑ፤ ሁሉም ማህበረሰብ ይህን እንቅፋት በተባበረ ክንድ ማክሸፍ እንዳለበትም አሳስበዋል። ከጌዲዮ እውነተኛ እርቅ እና ይቅር መባባልም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ትምህርት ሊወስድ ይገባል የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2012
ዳግም ከበደ