የአሰፋ ሁሴን አባት ከሚወዱት ጓደኛቸው ጋር በመቀናጀት 3 መኪናዎችን ይገዛሉ።ሆኖም የአሰፋ እናት ንብረቱን ወደግላቸው እንዲያዛውሩ በመጎትጎታቸው አባትዬው በሀሳቡ ተስማምተው ገንዘባቸውን አሟጠው ለአጋራቸው ይሰጡታል።ግን ብዙም ሳይቆዩና ንብረቱን ሳይረከቡት በሂደት ላይ ሳሉ ያስገድላቸዋል።በዚህም ቤተሰቡ ችግር ውስጥ ይወድቃል።
መልካም ማሰብ ጥሎ ባይጥልም እኔን ግን ብዙ ዋጋ አስከፍሎኛል የሚሉት አቶ አሰፋ ፤ በአባታቸው ሞት ምክንያት በቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ መጥፋቱ፣እናት ልጆችን ለማሳደግ ያልቆፈረችው ድንጋይ አለመኖሩና እርሱ የአባቱን ደም ያልመለሰ ተብሎ ሚስት እንኳን ማጣቱ በጣም አሰቅቆት ያለፈው ጉዳይ መሆኑን ያነሳል።
‹‹እናቴ ሁልጊዜ መፈክሯ ክፉ ለዋለብህ ደግ ዋልለት ነው።በዚህም በአካባቢው እንደባህል የሚወሰደውን ደምን በደም የመመለስ ተግባርን ተቃውሜ ቆይቻለሁ›› የሚለው አቶ አሰፋ፤ የደም ነገር ቀዬውን አስለቅቆት በሰው አገር ተንገላቶ እንዲኖር እንዳደረገውም ይናገራል።
ደምን በደም የመመለስ ጉዳይ ዝምታ ከበዛበት እንኳን ያስጠይቃል የሚሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህርና የግዮን በጎ አድራጎት ማህበር ሥራ አስኪያጅ አራጋው ገበዬ ናቸው።እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ቂም በቀል ህመሙ መቼም አይለቅም::ግን ሌሎችን ለማትረፍ የዛሬን ከባድ ህመም መተው ይበጃል።በዚህም እኛ እየተሳካልን ነው።በአማራ ክልል ጎንደር ወረዳዎች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ብዙ ለውጥ አምጥተናል።
በአካባቢው ጥቁር ደም እየተባለ የገዳይን ቤተሰብ ባገኙት ልክ መልስ የሚሰጡበት ልምድ መኖሩን የገለጹት መምህር አራጋው፤ ይህ ሁኔታ ለሰላምና ደህንነት አስጊ ነገሮችን እየፈጠረ ነው።ብዙዎች ባልሰሩት ተግባር ህይወታቸው እያለፈም ነው።ስለዚህም የደም ውርስን ለማስቀረት በማህበረሰቡ የተመረጡ እንዲሁም ማህበረሰቡ እምነት የጣለባቸውን 103 ግዮናዊ ሸምጋዮችንና 49 አመቻች ወጣቶች ሰልጥነው እየሰሩ ይገኛሉ።ይህ ደግሞ በራስ ተነሳሽነትም ደም የሚያቃባውን እንዲያ ቆም እድል እየሰጠው መሆኑን ይናገራሉ።
በግዮን ሽማግሌዎች ባህላዊ ፍትህ ወይም እርቅ እየተከናወነ እንደሆነ የሚገልጹት መምህሩ፤ ድርጊቱ በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች ይፈጸማል።ስለሆነም ባለፈው ዓመት ብቻ በጎንደር አካባቢ 187 ከፍተኛ የሚባሉ በቂም በቀል ደም ለመመለስ ይፈፀም የነበረን ችግር በሰባት ወረዳዎች ላይ መፍታት ስለቻልን ደስተኞች ነን ይላሉ።
እንደ መምህር አራጋው ገለጻ፤ ከባድ ችግሮች ደም ሳይቃቡ እንዲፈቱ የሆነው ግንዛቤ በማስጨበጥና ማህበረሰቡ አምኖ የመረጣቸው ሽማግሌዎች ያመኑበትና የኖሩበትን ባህል እንዲተው ስላደረጋቸው ነው።በመሆኑም አሁንም ቢሆን ማህበረሰቡ በርካታ የሰላም ማበልፀጊያ ባህላዊ ሥርዓቶች አሉትና ሊጠቀምበት ይገባል።
ደም መመለስ የሚለው ጉዳይ ሥር የሰደደ መሆኑን የሚያነሱት ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህርና የጎንደር ባህል ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ገብረማርያም ይርጋ ሲሆኑ፤ አዕምሮ ልማት ላይ መሥራት እንደሚገባ ይናገራሉ።ሀገር ሰላም እንድትሆን ይህንን ማድረጉን ማበረታታት እንደሚገባም ያስረዳሉ።
‹‹ይህ ሥራ በአርማጮኽና ጠገዴ አካባቢ ያሉ ችግሮችን ከመፍታት አኳያም ትልቅ ድርሻ ነበረው›› የሚሉት መምህር ገብረማርያም፤ በደም መቃባት ምክንያት ሰው የማይኖርበት አካባቢ እየተፈጠረ መሆኑን ያነሳሉ።ዛሬ የሽምግልናው ተስፋ ማበብ ካልቻለም ችግሩ አገር እስከማውደም የሚደርስ መሆኑን ይናገራሉ።
ዛሬ ዛሬ ማህበረሰባችን በፖለቲካው ያለው ተሳትፎ እየጨመረ በሰላም እሴት ግንባታ ላይ ደግሞ እየቀነሰ መጥቷል።በዚህም ሽምግልናው ቦታውን ለፖለቲከኛው እንዲለቅ አድርጎታል።ስለዚህ መንግስት መበቃቀል እንዳይኖር የሚያደርጉ አባቶችን ማበረታታት ላይ መስራት እንዳለበት ያስረዳሉ።ሽማግሌዎችን እንዲበረቱ የሚያግዙ ተቋማትንም ማስፋት ይገባዋል ይላሉ።
የተማረው ሰው የተመቻቸ ቦታ ላይ ቆሞ ‹‹በለው ጣለው›› እያለ ባለበት በዚህ ጊዜ አገርን ለማዳን ከሽማግሌዎች ውጪ አማራጭ እንደሌለ የሚናገሩት ደግሞ በሀድያ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት የባህል፣ ታሪክና ቅርስ ጥናትና ልማት ዳይሬክተር አቶ መለሰ ገብሬ ናቸው።እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በሀድያ ብሄረሰብ የደም በደም መልስ በስፋት ይከናወናል።ሆኖም በሽማግሌዎች አማካኝነት ከ75 እስከ 80 የሚሆኑ ችግሮች ይፈታሉ።ይህ ደግሞ ዳግም በቀል በማይመጣበት ሁኔታ የሚደረግ ነው።
በሀድያ ባህል ጢጉላ የሚባል ሥርዓት ያለ ሲሆን፤ ደምን በደም ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ መለሰ፤ በባህላችን ሽምግልና የማይፈታው ነገር የለም።ለእነርሱም አልገዛም ማለት ክልክል ነው።ስለዚህም የተቃረነው ቤተሰብ እንዲሆን እድል የሚፈጥር በመሆኑ ይህ ተግባር በሁሉም አካባቢ መቀጠል አለበት ይላሉ። ሰው የሚያስፈልገው ቦታ ደርሶ ሰላም መፍጠር ለነገ መባል እንደሌለበት አስረድተዋል።
አንዳንድ ጊዜ አርአያ የሆነ ሰው ስህተት ሊሰራ ይችላል።ሆኖም የግለሰቡን ማንነት ሳይሆን የሀሳቡን ጠቀሜታ በመመልከት የአባቶችን ምክር እየሰሙ ለአገር ሰላም መረጋገጥ መስራት እንደሚገባም ይገልጻሉ።ደም በደም አይደርቅምና የተጣላን ሁሉ በፍቅር በማሸነፍ የአገር ሰላምን ለማረጋገጥ በአማራ ክልል የተጀመረውን ሥራ በሁሉም ክልሎች ማስፋት ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው