አዲስ አበባ:- በስድስት ወራት ውስጥ ከማዕድንና ነዳጅ ኢንቨስትመንት 18 ነጥብ 752 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ። በስድስት ወራት ውስጥ 1ሺ 649 ነጥብ 8 በርሜል ነዳጅ የሙከራ ምርት በማምረት ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ 55ሺ 994 ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።
ሚኒስቴሩ ትናንት የመጀመሪያውን መንፈቅ ዓመት የስራ አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣው መግለጫ ላይ የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መክብብ መስቀለቃል በመድረኩ እንደገለጹት፤ በስድስት ወራት ውስጥ ከማዕድንና ነዳጅ ኢንቨስትመንት ከኩባንያዎች ምርት ሽያጭ ዘጠኝ ነጥብ 987 ሚሊዮን ዶላር እና ከባህላዊ አምራቾች ምርት ሽያጭ ስምንት ነጥብ 781 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 18 ነጥብ 752 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ተገኝቷል።
ከማዕድንና ነዳጅ ኢንቨስትመንት የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከእቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በባህላዊ መንገድ 63 ነጥብ 51 ሚሊዮን ዶላር ታቅዶ ስምንት ነጥብ 781 ሚሊዮን ዶላር የተገኝ ሲሆን፤ በኩባንያ ደግሞ 20 ነጥብ 45 ሚሊዮን ዶላር ታቅዶ ዘጠኝ ነጥብ 987 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል።
ከዕቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ ዝቅ ያለበትን ምክንያት እንዳብራሩት፤ የክልሎች ቁርጠኝነት ማነስ ፤በባህላዊ መንገድ የሚመረቱ ማዕድናት ላይ ቁጥጥርና ክትትሉ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ አለመውረዱና በዚህም የተነሳ ወደ ባንክ ሳይገባ በህገወጥ መንገድ መሸጡና እና ስራ ያቆሙ ኩባንያዎች ችግራቸውን ፈትቶ ቶሎ ወደ ስራ እንዲመለሱ አለመደረጉ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል በሶማሌ ክልል ሂላላ በተባለ ልዩ ቦታ 1ሺ 649 ነጥብ 8 በርሜል ነዳጅ የሙከራ ምርት በማምረት ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ 55ሺ 994 ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን የተቻለ ሲሆን፤ በባህላዊ አምራቾችና በኩባንያዎች አማካኝነት የተለያዩ ማዕድናትን ለአገር ውስጥ ሽያጭ በማቅረብ በስድስት ወራት ውስጥ 265 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማድረግ ታቅዶ 364 ነጥብ 76 ሚሊዮን ብር ገቢ ተደርጓል። በዚህም አፈጻጸሙ ሰባት በመቶ ከፍ ማለቱን አመልክተዋል።
እንዲሁም በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት 17 ፈቃዶችን በማዕድን ዘርፉ ለመስጠት ታቅዶ 20 ፈቃዶች (13 የምርመራና 7 የምርት) የተሰጡ ሲሆን፤ በስድስት ወራት ውስጥ በተሰጡት 20 ፈቃዶች 0.52 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ማስመዝገብ ተችሏል። በተጨማሪም በነባር ፈቃዶች 0.482 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ካፒታል ስራ ላይ መዋሉን ተናግረዋል።
አጠቃላይ የምርመራና የምርት ፈቃዶችን የማጥራትና ያሉበትን ደረጃ በጥልቅ ጥናት በማከናወን የማስተካከያ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ በስድስት ወራት ውስጥ በነባር ኩባንያዎች አማካኝነት 813 እና ከአዳዲስ ባለፈቃዶች 583 የስራ ዕድሎች የተፈጠሩ ሲሆን፤ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች አማካኝነት ደግሞ 61ሺ 802 የስራ ዕድሎችን መፍጠር ተችሏል። ይህም ከዕቅዱ አንጻር በኩባንያዎች በኩል አፈጻጸሙ ከፍ ያለ ሲሆን በክልሎች በኩል ያለው አፈጻጸሙ ዝቅ ማለቱን እንደሚያሳይ ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ሶሎሞን በየነ