ነሐሴ 10 ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው አምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ፓርቲዎች የየራሳቸውን ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው። አብዛኞቹ በየክልሉ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን በመክፈት ስራ ላይ ተጠምደዋል። ሌሎቹም አባሎቻቸውን በመመልመል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ። በዚህ ሂደት ታዲያ ጥቂት የማይባሉት ፓርቲዎች ፅህፈት ቤቶቻቸውን በመክፈት ሂደትም ሆነ ስብሰባ ለማካሄድ ከፍተኛ ችግር እያጋጠማቸው እንደሆነ ይገልፃሉ።
በአንዳንድ ክልሎች በተደራጁ ሃይሎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማወክና ለመግታት ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን ያነሳሉ። እነዚህ አካላት የሚያደርጉት ሁከትና ጫና ለማስቆም በፀጥታ ኃይሎችም ሆነ የክልል መንግስታት የሚደረገው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ደግሞ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ እንዳደረገው ይገልፃሉ።
ይህ ስብሰባዎችን የማወክና እንቅስቃሴን ለመግታት የሚደረግ ፀረ ዲሞክራሲ ተግባር አሳስቦናል ከሚሉ ፓርቲዎች መካከል የኢዜማ ፓርቲ አንዱ ነው። የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አንዷለም አራጌ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ችግሩ ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ መጥቷል። በተለይም በቅርቡ ጎንደር ላይ ፓርቲያቸው ሊያካሄደው የነበረው ስብሰባ በረብሻ እና በሁከት መቋረጡ የምርጫው ነፃና ፍትሃዊነት ላይ ትልቅ ጥያቄ አጭሯል።
የደረሰባቸውን ሲያስረዱ «እኔ በተገኘሁበት የጎንደሩ ስብሰባ የተደራጁ ወጣቶች ከውጭና ከውስጥ ሆነው ተሰብሳቢው ወደ አዳራሽ እንዳይገባ፤ ውይይትም እንዳናደርግ ከፍተኛ ጩኸት ያሰሙ ነበር። ጩኸታቸውን አቁመው እንድንወያይ ብንማፀናቸውም ፈቃደኛ ባለመሆናቸውና በመካከላችን መግባባት ሊፈጠር አልቻለም። ሁኔታ እየከረረ ሄዶ ወደ ነብስ መጥፋት እንዳይሄድ በሚል ስጋት ስብሰባውን ለማቋረጥ ተገደናል» ሲሉ ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
በጎንደር የነበረን ስብሰባ በማወክ ተግባር ላይ ስለተሳተፉ አካላት ማንነትም ሲያስረዱ«በአንድ በኩል የአብን አባላት፥ በስምና በአካል የሚታወቁ የወረዳው ሊቀመንበር ጨምሮ፤ ከክልሉ መንግስት በተለይም ከጥቃቅንና አነስተኛና ከንግድ ቢሮ የተላኩ እንዲሁም ደግሞ ከአማራ ወጣቶች ማህበር የመጡ ወጣቶች ይገኙበታል» በማለት ይጠቅሳሉ።
በተመሳሳይ በለሳና አምባጊዮርጊስ ላይ ስብሰባ አዘጋጅተው እንደነበር አቶ አንዷለም አስታውሰው፤ በዚያም እነዚሁ የተደራጁ ሃይሎች ስልታቸውን ቀይረው የልማት ስራ አለ በሚል ሰበብ ፓርቲው ባዘጋጀው ስብሰባው ላይ ህብረተሰቡ እንዳይገኝ ከፍተኛ ጫና በማሳደራቸው አብዛኛው ሰው ፈርቶ መመለሱን ነው የሚናገሩት። ይህ ስብሰባዎችንና እንቅስቃሴን የማገት ተግባር በደብረብርሃንና አርባ ምንጭ ላይ መከሰቱንና በዚህ ሁኔታ ፓርቲው ባሰበው ልክ ህዝቡ ጋር ለመድረስ እንደሚቸገር ያስረዳሉ።
በወቅቱ ከክልሉ የፀጥታ ኃይል ድጋፍ ለማግኘት ፓርቲያቸው ያደረገውን ጥረት ተጠይቀውም «የፀጥታ ኃይሎቹ ለምን ሰላም እንደማያስከብሩ ስንጠይቃቸው እናንተ ዛሬ ትሄዳላችሁ ነገ እኛ ሽፍት እንኳን የሚቀይረን በሌለበት ድንጋይ ቢወረወርብን የሚያድነን የለም ነበር ያሉን። እናንተ ስትሄዱ የሚደርስልን የለም ስለዚህ አንነካቸውም ነው ያሉት» በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ አንዷለም በጎንደር ካጋጠማቸው ችግር ጋር ተያይዞ ከአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ጋር ለመወያየት ጥረት ቢያደርጉም የክልሉ ፕሬዚዳንት አዳማ ለስብሰባ በመሄዳቸው ምክንያት ሳይሳካላቸው መቅረቱን ነው የገለፁት። ችግሩ እንደተከሰተ ፓርቲው ቅሬታቸውን ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ መግለፁን አቶ አንዷለም አመልክተው እስካሁን ግን ከቦርዱ የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩን ይጠቁማሉ።
«ይህ ሁኔታ በድምሩ የሚያሳየን የመንግስት አካላት እጃቸው እንዳለበት ነው» የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ፓርቲያቸው በመንግስት በኩል ምህዳሩን ለማስፋት እርምጃ ይወሰዳል ብሎ ቢያስብም ከታች ያሉ አመራሮች በጎ ፍቃዳቸውን እያሳዩ አለመሆኑ እንዳሳዘናቸው ይጠቅሳሉ። «ከታች ያሉት አካላት አሁንም ያለመለወጥና ገና በነበረው መንገድ የመጓዝ ፍላጎት እንዳላቸው አመላካች ነው» በማለት ይገልፃሉ።
እንደ አቶ አንዷለም ማብራሪያ አሁን ያለው ለውጥ እንዲመጣ የፓርቲው አባላት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል። ለውጡ ከመጣ በኋላም እውነተኛ ዴሞክራሲ ይሰፍናል በሚል ተስፋ የበኩላቸውን ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይሁንና አንዳንድ የመንግስት ኃላፊዎች በተለይም በክልሉ ያሉ አመራሮችና ካድሬዎች የምርጫ ወሬ ሲሰማ እንደቀድሞው ሁሉ ከፓርቲዎች ጋር ትንቅንቅ ጀምረዋል።በአገራዊ ጉዳይ ላይ በሁሉም ክልል ተንቀሳቅሶ መወያየት አዳጋች ሆኗል። በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ምርጫውን ለማካሄድ ቀርቶ ተግባብቶ አገሪቱን ለማስቀጠል አስቸጋሪ ይሆናል ብለዋል።
በመሆኑም በመንግስት አመራሮች ሳይውል ሳያድር ቁርጠኝነታቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባ አቶ አንዷለም ያስገነዝባሉ። የአንድ ምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ዴሞክራሲ እንዲመጣ ሁሉም የሞተለትና ዋጋ የከፈለበት በመሆኑ የፓርቲዎችን እንቅስቃሴዎችን የሚያውኩ የተደራጁ ሃይሎችን በአፋጣኝ ማስቆም እንደሚገባም ያሳስባሉ። የፀጥታ ኃይሉም ለቆመለት ህገመንግስትና ህዝብ ታማኝ በመሆን ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ነው አቶ አንዷለም ጥሪያቸውን ያስተላለፉት።
የነፃነት እኩልነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አብዱልቃድር አደም በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው በተለያዩ አካባቢዎች ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤቶችን ለመክፈት በሚያደርገው ጥረት በተወሰኑ አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግር ያጋጠመው መሆኑን ይገልፃሉ። «በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ የማዋከብ ነገር አጋጥሞናል። ስብሰባ ለማካሄድ ሆቴሎች ጋር ስምምነት ፈጥረንና ገንዘብ ከፍለን እያለ አንድ ቀን ሲቀረው ባልታወቀ ምክንያት አዳራሹን እንደማይፈቅዱልን ይነግሩናል» በማለት ይናገራሉ።
አንዳንዶቹም በግልፅ ከክልሎቹ አመራሮችና ደህንነቶች ማስፈራሪያ የደረሳቸው በመሆኑ ዝግጅቱን ማካሄድ እንደማይችሉ የሚነግሯቸው መሆኑን ዶክተር አብዱልቃድር ያስረዳሉ። አንዳንድ ጊዜ ተፅዕኖው ከገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ውጭ የሚሆንበት አጋጣሚም መኖሩን ያመለክታሉ። «ግለሰቦችና ቡድኖች የሚፈጥሩት ጫና ሰራዎችን እንዳናከናውን ተደርገናል» በማለት ተናግረው፤ በመሆኑም መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድተው አስፈላጊውን ቁጥጥርና ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መስራች አባል አቶ መኮንን ዘለለው ደግሞ አንዳንድ የሕወሃት አመራሮችና ፓርቲያቸው በክልሉ ተንቀሳቅሰው ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤቶችን ለመክፈትም ሆነ ለአባላቶቻቸው ስብሰባ ለማካሄድ ከፍተኛ ተፅእኖ እየፈጠሩባቸው መሆኑን ይናገራሉ። «በሕወሃት አመራሮች የሚደርስባቸውን ዛቻና ጫና በመፍራት ሆቴሎችም ሆነ ግለሰቦች አዳራሾችና ቤቶቻቸውን ለእኛ ማከራየት አይፈልጉም» በማለት ቅሬታቸውን ያቀርባሉ። በክልሉ ያሉት መገናኛ ብዙሃኖችም በሙሉ በሕወሃት ስር ያሉ በመሆናቸው ቅሬታቸውን ህዝቡ እንዲያውቀው ማድረግ እንኳ አለመቻላቸውን ያስረዳሉ።
«ይህ በሆነበት ሁኔታ ፍትሃዊና ነፃ ምርጫ ለማካሄድ እንቸገራለን። መንግስትም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ ክልል ህዝብ በምን ያህል ጫና ውስጥ እየኖረ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል» በማለት አቶ መኮንን ይናገራሉ። በመሆኑም የፌደራል መንግስትና ምርጫ ቦርድ ፓርቲያቸው ህዝቡን ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለባቸውም ያስገነዝባሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ማህሌት አብዱል