ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት። የኑሮ ውድነት፤ ሥራ አጥነት፤ የጸጥታ ችግር፤ጽንፍ የወጣ ብሄርተኝነትና የሃይማኖት አክራሪነት እና ውሉ ያልታወቀው የ2012 ምርጫና የደቀነው ስጋት አፍጥጠው የመጡ ችግሮቻችን ናቸው።
በተለይም ምርጫ 2012 ይካሄድ አይካሄድ የሚለው የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዜጎች ሃሳብ እንዳለ ሆኖ ከወዲሁ የሀገርን ህልውና ስጋት ውስጥ የሚከቱ ድርጊቶች እየታዩ ነው። የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተናጠል የምርጫው መካሄድና አለመካሄድ ላይ ጽንፍ የያዘ አቋም በመያዝ የራስን ስሜት በመከተል ብቻ የሀገሪቱን ዕጣ ፋንታ ሲወስኑ ይደመጣሉ። ምርጫው ካልተካሄደ ሀገር ትፈርሳለች፤ የራሳችንን መንግስት ለመመስረት እንገደዳለንና መሰል የጥፋት ንግርቶችን ማዳመጥ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አፍ ሰርክ የሚወጣ አዋጅ ነው።
በሌላው ወገን ደግሞ ምርጫውን ለማካሄድ በሀገሪቱ ያለው ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ አይደለም፤የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው ከደጋፊዎቻቸው ጋር መወያየት በማይችሉበት ሁኔታ ምርጫውን ማካሄድ አይቻልም፤መንግስት ምርጫውን ተከትሎ የሚመጣውን ቀውስ ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም ስለሌለው ምርጫው መካሄድ የለበትም፤ከተካሄደ ያልቅልናል የሚሉ ሙሾዎችም ቢያንስ በቀን ሳንሰማ አንውልም።
በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይነጋገሩ፤ሳይወያዩና ሳይደማመጡ በተናጠል መፍትሄ ፍለጋ ላይ ሲሮጡ ይታያሉ።ውይይት፤መደማመጥና መነጋገር በሌለበት መተማመን ከየትም ሊመጣ አይችልም። በየትኛውም ፓርቲ የሚነሱት ሀሳቦችና ስጋቶች እውነትነት ይኑራቸውም አይኑራቸውም ችግሮችንና ስጋቶችን በተናጠል ከመወርወር እና ህዝብን ጭንቀት ውስጥ ከማስገባት ባለፈ በጋራ ችግሮች ላይ ቁጭ ብለው ሲመካከሩ አላየንም።
የፖለቲካው ተዋናዮች ችግሮችን አስቀድመው በመተንበይና ሁነኛ መፍትሄ በማምጣት ሀገርንና ህዝብን ከጭንቀት መገላገል ሲገባቸው እራሳቸው ጭንቀት ሆነውብናል። ህዝብ የተደራጀ ኃይል ባለመሆኑ ያሉትን ሀገራዊ ችግሮችና ስጋቶችን ፈር የማስያዝና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ብያኔ ለመስጠት አይችልም። ይህ በዋነኝነት መንግስት ጨምሮ በፖለቲካው ውስጥ የሚሳተፉና ያገባኛል የሚሉ አካላት ዋነኛ ስራ መሆን ነበረበት። እንደ መርዶ ነጋሪ በየቀኑ ብሶቶችና ስጋቶችን እየነገሩ ህዝብን ማሳቀቅ ብቃትንም፤ ዕውቀትንም የሚጠይቅ አይደለም።ይልቁንም አሁንም ባለችው አጭር ጊዜ ቢሆን የፖለቲካው ተዋናዮች ካሉበት መርዶ ነጋሪነት ወጥተው በችግሮቻችን ዙሪያ ቁጭ ብለው ሊመክሩ ይገባል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቁ ጉድለት የመነጋገር ባህል አለመለመዱ ነው። ተፎካካሪን እንደ ጠላት ማየትና ማሳደድ ለዓመታት የተፀናወተን ልማድ ነው። በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረው የጋራ ችግሮችን ለመፍታት ከሚጥሩ ይልቅ የፌስ ቡክና ወሬና አሉባልታ ይበትናቸዋል።ሀገሪቷ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ የሚያወጣ ፍቱን መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የሀገሪቱን መበተንና መፈራረስ የሚያውጅ መርዶ መናገር ይቀላቸዋል።
መደማመጥ በሌለበት መተማመን ስለማይኖር ሀገራዊ ችግሮች የመፍትሔ ያለህ እያሉ ዓመታት ይነጉዳሉ። ስለዚህም በእጃችን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ከዳር ለማድረስና በተለይም መጪው ምርጫ ሀገራዊ ሰላም እንዲኖረውና ሕዝቦችም ከስጋት ነጻ እንዲሆኑ ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚሉ አካላት በሙሉ ውይይትንና መደማመጥን መርሃቸው ያድርጉ።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2012