አዲስ አበባ፡- በቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የመጀመሪያ የሆነው የመድኃኒት ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የፋብሪካው ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
የፋብሪካው ሸሪክና የአፍሪኪዩር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ተፈሪ የፋብሪካውን መገንባት አስመልክቶ ትላንት የመሠረተ ድንጋይ ሲያስቀምጡ እንደተናገሩት፤ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ አፍሪኪዩር ፋርማሲ ዩቲካል ማኑፋክቸሪንግ የተባለው የመጀመሪያው የመድኃኒት ማምረቻ ፋብሪካ በ10 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ኢንቨስትመንት ይገነባል፡፡
ፋብሪካው በአገር ውስጥና በውጭ ባለ ሀብቶች ጥምረት የሚገነባና ምርት ሲጀምር ለ109 ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፤የስራ ዕድል ከሚፈጠርላቸው ዜጎች 95 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ የውጭ ዜጎች ይሆናሉ፡፡ በሂደት የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያውያንን በማሰልጠን የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ኢትዮጵያውያን በሁሉም ደረጃ ማስተዳደር የሚችሉበት ፕሮግራም መቀረጹን አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፋርማሲዩቲካል ሴክተር በአሁኑ ወቅት በአማካኝ 25 በመቶ ገደማ እያደገ ይገኛል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ሆኖም በቂ አገራዊ የመድኃኒት ምርት በሌለበት ሁኔታ በፍጥነት የሚያድግ ፍላጎት አገሪቱን ላቅ ላለ የውጭ ምንዛሬ ጫና እንደሚያጋልጥና፤ የሚገነባው ፋብሪካ ደግሞ ጫናውን በማስቀረት ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች እንደሚተካና የውጭ ምንዛሬን እንደሚያስገኝ አስረድተዋል። በቴክኖሎጂ ሽግግር የአገሪቷን የቴክኖሎጂ እድገት እንደሚያግዝም ገልጸዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ ፋብሪካው የመሠረት ድንጋዩ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ ከ18 እስከ 24 ወራት ባልዘለለ ጊዜ ምርቱን ማቅረብ ይጀምራል። ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምር፤ በዓመት በአንድ ፈረቃ አንድ ቢሊዮን የሚሆን በአፍ የሚወሰድ እንክብል መድኃኒቶችን እንዲሁም 14 ሚሊዮን ጠርሙስ በሽሮፕ መልክ የሚዘጋጅ መድኃኒቶችን የማምረት አቅም ይኖረዋል። በድርጅቱ ውስጥም ሴቶች ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙኒር ካሳ በበኩላቸው፤ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሞተው ህዝብ 57 በመቶ የሚሆነው ሰው በ‹‹ኢንፌክሽን›› በሚከሰቱ በሽታዎች እንደሚሞት በመግለጽ፤ ፋብሪካው ከሚያመርታቸው መድኃኒቶች ለእነዚህ በሽታዎች የሚውሉ እንዳሉ ጠቁመው፤ ይህም ለአገሪቷ ዜጎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። በሽታ ከመከላከል አንጻርም ጥራት ያለውን መድኃኒት በወቅቱ ለማቅረብ ሚናው የጎላ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ለዜጎቿ ሙሉ የሆነ የጤና ሽፋን ከመስጠት ባለፈ በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን ተግታ እየሰራች መሆኗን ጠቅሰው፤ የግንባታው መካሄድ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታት ወደ ሥራ እንዲገቡና ለሰውና ለእንስሳት የሚሆኑ መድኃኒቶችን የማምረት ሂደትን ለማስፋፋት አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የአገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ ባለሀብቶች በተገኙበት የፋብሪካው ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ትላንት በቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ተቀምጧል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2012
አዲሱ ገረመው