አዲስ አበባ፡- በ2008 ዓ.ም በተተገበረው የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት ፕሮጀክት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ መባከኑ ተገለጸ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ ከኃላፊነታቸው ከመነሳታቸው በፊት ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል እንዳሉት፣ ትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ገንዘብና ሚኒስቴር በሁለት አመታት ውስጥ ፕሮጀክቱ እንዲጠናቀቅና ገንዘቡ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በሚል የመጣ ፋይናንስ እንደነበረ እያወቁ ለመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ገንዘቡን ባለቀ ሰዓት አስረክበዋል። በዚህ የተነሳ በቂ ጥናት ሳይደረግበት፤ አመራሩ ኃላፊነት ላለመውሰድ በችኮላና በጥድፊያ እንዲያልቅ በመፈለጉ ገፍተር ገፍተር ተደርጎ ገንዘቡ ከእጅ እንዲወጣ ተደርጓል፤ በዚህም ለብክነት ተጋልጧል፤ አመራሩም በቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ገፍቶ ለማገዝ ድፍረት አልነበረውም።
ዶክተር ሰለሞን፣ ስራው ከተጀመረ በኋላም የሚገጥሙ ችግሮችን ‹‹እንደነገሩ አድርጋችሁ ጨርሱ›› የሚል አቅጣጫ እየተቀመጠ ስራው መሰራቱን ገልጸዋል። በመጨረሻም ብስክሌቶች በውድ ዋጋ(ያንዱ ዋጋ እስከ 35 ሺህ ብር) ተገዝተው ለማህበራት መታደላቸውን አስረድተዋል። ብስክሌቶቹ አርጅተው ወላልቀዋል፤መለዋወጫ ሆነዋል፤ ማህበራቱም የተበተኑ አሉ፤ ፕሮጀክቱም የከሰረ በመሆኑ ከዚህ ልምድ ሊወሰድበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በቃሉ፣ሳሙኤልና ጓደኞቻቸው የብስክሌት ትራንስ ፖርት አገልግሎት ሕብረት ስራ ማህበር በሰሚት ‹‹ሳይት›› አስር አባላት ይዞ በቦሌ ወረዳ ስምንት ጥቃቅንና አነስተኛ ጽሕፈት ቤት አማካኝነት የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ከተደራጁት አንዱ ነው። የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል አስረስ እንደሚለው፣ ፕሮጀክቱ የተጀመረው አያት፣ሰሚት እና ቦሌ እንዲሰሩ በተደራጁ ሶስት ማህበራት ነው። በአጠቃላይ 210 ብስክሌቶች ለሶስቱ ማህበር
እንደቀረቡላቸው እና የወጣባቸው ወጪም ሰባት ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተናግሯል።ለእያንዳንዱ ማህበር 70 ብስክሌቶች(ዋጋቸውም ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን) እንደደረሳቸውም አቶ ሳሙኤል አስረድቷል። የመለዋወጫ፣ የመቆጣጠሪያ እና የመገናኛ እቃዎች ይሰጣሉ የተባልን ቢሆንም ሳይሰጠን ቀርቷል የሚለው አቶ ሳሙኤል፣ በዚህ የተነሳ ለመለዋወጫ 200 ሺህ ብር ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተበድረናል። 17 ብስክሌቶች ተሰርቀዋል፤48 ወላልቀው አልቀዋል፤ አሁን በስራ ላይ የሚገኙት ብስክሌቶች አምስት ብቻ ሲሆኑ አባላቱም የቀሩት አምስት እንደሆኑ ተናግሯል።
‹‹የእኛ ማህበሩ በነፍሱ አለ፤ አያትና ቦሌ ላይ የተደራጁት ተበትነው ከጠፉ አመታት ተቆጥረዋል›› ሲልም አክሏል። ለኪሳራ የተዳረጉት በቁጥጥር ችግር እና በቅድመ ጥናት ችግር እንደሆነ ገልጿል። መንግስትን ላለመክዳት ስንል እዳ ውስጥ ገብተን የአገር ውስጥ መለዋወጫ ብንገዛም ተጠቃሚ ልንሆን አልቻልንም ሲልም አማርሯል።
በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ ስምንት ዲስትሪክት አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ንኡስ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ተመስገን ብስክሌቶቹ ከሞላ ጎደል ሁሉም በሚባል ደረጃ በቆሙበት ሁኔታ ተጨማሪ ብድር በምን አግባብ ሊያገኙ እንደቻሉ ሲገልጹ፣ ‹‹የተፈቀደላቸው ስራቸውን አስፋፍተው እንዲሰሩ ነው። ክትትል እየተደረገላቸው ነው። ከወሰዱት ብድር 53 ሺህ 333 ብር መልሰዋል። 46 ሺ ብር የሚኖርባቸው ቢሆንም ከ60 ሺ ብር በላይ የቆጠቡ በመሆናቸው ስጋት የሚፈጥር አይደለም›› ብለዋል።
በአዲስ አበባ ቦሌ፣አያትና ሰሚት አካባቢዎች በብስክሌት ተደራጅተው የተሰማሩ ሁሉም ማህበራት በየወሩ 22ሺህ 975 ብር በመክፈል በ58 ወራት እዳቸውን ከፍለው እንደሚያጠቃልሉ በቢዝነስ ፕላኑ ተመላክቶ እንደነበር ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2012
ሙሐመድ ሁሴን