አዲስ አበባ፡- የአረቢካ ቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ባላት የቡና ሀብት ልክ ተጠቃሚ ያልሆነችበትን የአሰራር ሂደት ለመቀየር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ። ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽን እያካሄደች ነው።
ኢትዮጵያ ለ2ኛ ጊዜ ያዘጋጀችውን ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽን ትናንት በሚሊኒዬም አዳራሽ በይፋ ያስጀመሩት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሀሰን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ሰፊ የቡና ሀብት ያላት ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ግን ተጠቅማለች ማለት አይቻልም። በመሆኑም ይሄን ገጽታ መቀየርና የዘርፉን ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አሰራሮችና ተግባራት ይከናወናሉ።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ለምግብ ዋስትናዋ፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ግብዓቷ እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ግኝቷ ጭምር አሁንም በግብርናው ላይ የተመሰረተ ነው። ቡና ደግሞ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ነው፤ ከኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ግኝትም ከ45 እስከ 50 በመቶ ድርሻ ይይዛል።
አሁንም በሚፈለገው ልክ ኢትዮጵያ ከዘርፉ ተጠቃሚ ሆናለች ስለማይባል የቡና ልማትና ምርታማነትን በቀጣይ አምስት ዓመት በሶስት እጥፍ የማሳደግ እቅድ መያዙን ያመለከቱት ሚኒስትሩ ፤ የገበያ ስርዓቱን ለማዘመንና አምራቾች ጭምር በቀጥታ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡበትን እድል ለመፍጠር ይሰራል፤ የቡናው ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ ይደረጋል፤ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩም ድጋፍ ይሰጣል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንደሚሉት፤ የቡና ሃብት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መሰረት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መስተጋብር ማሳለጫ የባህል ሰንሰለት ነው። የከባቢ ሚዛን መጠበቂያ አረንጓዴ ሀብትም ነው። ይሁን እንጂ አንድም ቡናን በብዛትም በጥራትም ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ጋር በተያያዘ፤ አንድም የቡና ምርቷ የራሱ መለያ ሎጎ ይዞ ካለመቅረቡ ጋር በተገናኘ ከሃብቷ መጠቀም ባለባት ልክ እንዳትጠቀም አድርጓታል። በመሆኑም ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ከመባል ባለፈ ካላት የቡና ሀብት ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
የቡና ፓርክ ግንባታ የሚከናወን መሆኑን የገለጹት ዶክተር አዱኛ፤ኢትዮጵያ ምርቷን በዓለምአቀፍ መድረኮች የምታስተዋውቅበት ወካይ ብራንድ ሎጎም ተዘጋጅቷል። እነዚህ ተግባራት ደግሞ አንደኛ ቡናን በጥሬው ከመላክ ባለፈ እሴት ጨምሮ ለመላክ እድል የሚሰጥ ሲሆን፤ ሁለተኛም አንዳንድ ተቋማት የኢትዮጵያን ቡና ከሌላ ቡና ጋር እየቀላቀሉ የሚሸጡበትንና በኢትዮጵያ ቡና ጣዕም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አካሄድ በማስቀረት የላቀ ተጠቃሚ የሚያደርጋት ይሆናል። ቡናን በጥራትና በብዛት አምርቶ ማቅረብን፤ በፖሊስና የህግ ማዕቀፍ መታገዝን የሚፈልግ ሲሆን፤ ለዚህም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገዝበዋል ።
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጀና በበኩላቸው እንዳሉት፤ ቡና በኢትዮጵያ የውጭ ገበያ ጉልህ ድርሻ ያለውና ለኢኮኖሚዋም የጀርባ አጥንት ነው። ሆኖም በአግባቡ ካለማስተዋወቅም ሆነ ሌሎች ችግሮች ምክንያት የሚፈለገውን ያክል ለውጭ ገበያ ቀርቦ መጥቀም ባለመቻሉ ይሄን ገጽታ የሚቀይር ስራ መከናወን ይኖርበታል። ከዚህ አኳያ ዓለምአቀፍ የቡና ኤግዚቢሽኖች ደግሞ የቡና አምራችና ላኪዎችን ከገዢዎች ጋር ለማገናኘት፣ የቡና ሀብቱን ለማስተዋወቅ፣ ፍትሃዊ የቡና ንግድ ተጠቃሚነትን ለማምጣት፣ የቡና አመራረት ተሞክሮን ለመለዋወጥ፣ ነባር ገበያዎችን ለማቆየትና አዳዲስ ገበያዎችን ለመድረስ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
ኢትዮጵያ 684ሺ ሜትሪክ ቶን ቡና በማምረት ከአፍሪካ ከፍተኛ የቡና አምራች አገር ስትሆን፤ አብዛኛውን ምርቷንም ለአውሮፓ፣ አሜሪካ እና ጃፓን ገበያ ታቀርባለች። ይሄም ኢትዮጵያን አስር ከፍተኛ የቡና አምራችና ላኪ አገራት መካከል በአምስተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። ለምሳሌ፣ እኤአ በ2013 የምርት ዘመን 300ሺ ሜትሪክ ቶን ቡና ያመረተች ሲሆን 125ሺ ሜትሪክ ቶን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ችላለች። በተመሳሳይ በ2018 የምርት ዘመን 500ሺ ሜትሪክ ቶን አምርታ 231ሺ ለውጪ ገበያ ማቅረብ ችላለች።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2012
ወንድወሰን ሽመልስ