በኢትዮጵያ የትኛውም አካባቢ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ንጹህ ውሃን የማግኘት ጉዳይ የማያልፉት ፈተና ሆኖ ዘልቋል። በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ውሃን ብዙ ኪሎ ሜትር ተጉዘው በመቅዳት ለሚፈልጉት ፋይዳ የማዋል ሀላፊነት ከትከሻቸው ለተጫነባቸው ሴቶች ደግሞ ችግሩን የማይገላገሉት ምጥ አድርጎባቸዋል። የሀገሪቱ መለያ አርማ የውሃ ማማ መሆኑ ሳይካድ በሌላኛው ጫፍ ደግሞ ቀላል የማይባለው ማህበረሰባችን ውሃ የተጠማ መሆኑ እስከመቼ? መፍትሄውስ ምን ይሆን?
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዳሉት ፤በኢትዮጵያ 25 ሚሊዮን ሕዝብ አሁንም ንጹህ የውሃ አቅርቦት የለውም። በገጠር የሚኖረው ማህበረሰብ በቀን 25 ሊትር ውሃ በነፍስወከፍ እንዲያገኝ በከተማ የሚኖረው ደግሞ ከ40 እስከ 100 ሊትር ውሃ በቀን ማግኘት እንዲችል እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው በዚህ ስሌት መሰረትም የከተማው ነዋሪ 68 በመቶ እና የገጠሩ ደግሞ 78 በመቶ የንጹህ መጠጥ ውሃ ማድረስ መቻሉን ይገልጻሉ።
አቶ አስራት ካሳዬ በአማራ ክልል ውሃ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የክልሉን ሕዝብ የውሃ አቅርቦት ለማሟላት አነስተኛ የውሃ ተቋማትን መገንባት፣የገጠር ባለ መስመር ውሃ ዝርጋታ እና የከተማ ውሃ አቅርቦት እየተሰራ ነው ይላሉ። በዚህም በ2011 ዓ.ም ከ15 በላይ የከተማ የውሃ ተቋማትና ከ5 ሺህ በላይ አነስተኛ የውሃ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ከአለም ባንክና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር በከተማ 24፣በገጠር 31 የውሃ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ከሆነ በአማራ ክልል በከተማ 75 በመቶ በገጠር ደግሞ 88 በመቶ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ማድረስ ተችሏል። ከዚህ በፊት በገጠር አካባቢዎች ይሰሩ የነበሩት አነስተኛ የውሃ ተቋማት የእጅ ጉድጓድና ምንጭ ማጎልበት ሲሆኑ አሁን ላይ ግን ባለመስመር የሆኑ እስከ 15 ቀበሌዎችን የሚያገናኙ ትላልቅና ብዙ ሰዎች የሚይዙ በመሆናቸውና በቀን 25 ሊትር በሰው በመሆኑ ሽፋኑን ባልተለመደ ሁኔታ አሳድጎታል። በከተሞች በቀን 20 ሊትር በሰው የነበረው ስሌት አሁን ላይ ዝቅተኛው 40 ከፍተኛው ደግሞ 80 ሊትር አድጓል። በዚህ የተነሳ ሽፋኑ ከገጠሩ ማነሱን በምክንያትነት አስረድተዋል።
በክልሉ ከተሰሩ የውሃ ተቋማት ከ20 በመቶ በላይ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸው በቆጠራ እንደተረጋገጠ የተናገሩት አቶ አስራት፤ ይሄ ሁኔታ የተደራሽነት ሽፋኑን አሁን ከሚገኝበት ደረጃ ሊያሳንሰው እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል። የከርሰምድር ውሃ መቀነስና መድረቅ እንዲሁም የአየር ለውጥ መከሰትን በምክንያትነት አንስተዋል።
በክልሉ ውሃ ተደራሽ ያልሆነባቸው ወረዳዎችና ቀበሌዎች ምን ያህል እንደሆኑና የት አካባቢዎች እንደሚገኙ አዲስ ዘመን ላነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ እንዳሉት፤‹‹ ውሃ ተደራሽ ያልሆነባቸው ወረዳዎች ባይኖሩም ቀበሌዎች ግን አሉ። ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑት እንደ ምስራቅ በለሳ ያሉ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ውሃ የላቸውም። እስከ 60 ሜትር ተቆፍሮ ውሃ ማግኘት አልተቻለም። በዋግኽምራ አካባቢዎች ደግሞ እስከ 450 ሜትር ተቆፍሮ ውሃ ያልተገኘባቸው አካባቢዎች አሉ።በሰቆጣ ከተማ የተቆፈረውም ቢሆን ከታሰበው በታች በግማሽ ያነሰ ውሃ ነው በመስጠት ላይ የሚገኘው።ምክንያቱ ደግሞ የከርሰ ምድር ውሃ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ የተፈጠረ ነው።
በመፍትሄነት የተወሰዱት ርምጃዎችም ከከርሰ ምድር ውሃ ጥገኝነት በመላቀቅ የገጸ ምድር ውሃን መጠቀም ሲሆን በሰቆጣ አካባቢዎች ያሉ 16 ቀበሌዎች ጥናት ተጠናቅቋል።ስራውን በማፋጠን በሚቀጥለው አመት ውሃ ማግኘት እንዲችሉ እየተሰራ ነው። በምስራቅ በለሳ አካባቢዎች ደግሞ አሙሲትን ጨምሮ 17 ቀበሌዎችን የሚያገናኝ ዲዛይን ተጠናቅቋል በመሆኑም የከርሰ ምድር ውሃ ተጠቃሚ ይሆናሉ›› ሲሉ አቶ አስራት ካሳዬ አብራርተዋል።
በቀጣዮቹ አምስት አመታትም የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦቱ በከተማም ሆነ በገጠር ተደራሽ ይሆናል። ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ ቆላማ አካባቢዎች ደግሞ ከማህበረሰቡ ባለፈ ለእንስሳትም ጭምር የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦቱ የሚሟላ ይሆናል። ለዚህ ማስፈጸሚያም የሳውዲ መንግስትን ጨምሮ ከሌሎች ሀገራትና ድርጅቶች ከ600 ሚሊዮን ዶላር(USD) መገኘቱን ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2012
ሙሐመድ ሁሴን