አዳማ:- የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን አደረጃጀቱን መቀየሩ ገዳቢ ሆኖ የቆየውን አሰራሩን በማሻሻል የአካል ጉዳተኛውን ተጠቃሚነት እንደሚያሰፋው ተገለጸ።
የፌዴሬሽኑ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ዘነበች ኪዳነ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ የአካል ጉዳት ዓይነቶች ተብለው በተፈረጁ የጉዳት አይነቶች ብቻ ተሳትፎ ይደረግ ነበር፤ ይህ አካሄድ ገዳቢ ሆኖ ቆይቷል።
እንደ ወይዘሪት ዘነበች ገለፃ፤ አሁን ያለው አዋጅ ቁጥር 1113/2011 አካል ጉዳተኞች በመብታቸው ላይ ተደራጅተው እንዲሰሩና ሞጋች እንዲሆኑ የሚያበረታታ በመሆኑ እድሉን በመጠቀም የአካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽኑ አደረጃጀቱን ለመቀየር መወሰኑን አብራርተዋል።
አደረጃጀቱ በመቀየሩም በርካታ የአካል ጉዳተኞች አደረጃጀቶችን አቃፊ ሆኖ አገራዊና አለም አቀፋዊ ውክልናውን ከፍ ብሎ እንዲሁም የአባላቱን ጉዳይ በበላይነት እያስተባበረ መብታቸው እያስከበረ እንዲሄድ ከፍተኛ አቅም ይጨምርለታል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አደረጃጀት አንድ አካል ጉዳተኛ ወደ ፌዴሬሽኑ መቀላቀል ሲፈልግ እንደ ጉዳቱ አይነት ብሔራዊ ማህበራት መደራጀት ነበረበት ያሉት ወይዘሪት ዘነበች፤ ይህ በሙያ ማህበራት የተደራጁና በግላቸው የሚመጡ አካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ገድቦት መቆየቱን ጠቁመዋል።
ከሁሉም ክልሎች የተወከሉ የማህበሩ አባላት የተሳተፉበት ለሁለት ቀናት የሚቆይ የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን፤ አካል ጉዳተኞች በኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ከፍ የሚያደርግ ስልጠናም ይሰጣል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2012
እፀገነት አክሊሉ