አዲስ አበባ፡ የህብረት ስራ ማህበራትን ከኢኮ ኖሚ ጠቀሜታቸው ባለፈ ለሰላም ግንባታና የህዝብ ለህዝብ ትስስር መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ።
ሰባተኛውን ሀገር አቀፍ የህብረት ስራ ማህበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር መክፈቻ ስነ ስርዓት አስመልክቶ ትናንት በተካሄደው ሲምፖዚየም ላይ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲ ኡመድ እንደተናገሩት፤ የህብረት ስራ ማህበራት ዜጎች ሊፈቱት ያልቻሏቸውን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት ያስቻሉ ናቸው። እንዲሁም በብሄርና በሃይማኖት ሳይለያዩ በአንድነት እንዲሰሩና የጋራ ትስስር ለመፍጠር ከፍተኛ አቅም ስላላቸው በኢትዮጵያ የተጀመረውን ዲሞክራሲ ለማዳበርና የህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከሪያ መጠቀም ያስፈልጋል።
የህብረት ስራ ማህበራት ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት የመቆጣጠር አቅም እንዳላቸው አቶ አብዲ ገልጸው፤ ማህበራቱ የደረሱበትን የእድገት ደረጃ የሚመጥን ፤ የአባላትና የዜጎችን ገደብ የለሽ የመልማት ፍላጐት ማርካት የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠርና ያሉትንም የአሰራርና የአመራር ክፍተቶች በየደረጃው ማስተካከል ይገባል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ21 ሚሊዮን በላይ የህብረት ስራ ማህበራት አባላት ያፈሩ 89 ሺህ በላይ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት ያሉ መሆናቸውን አመልክተው ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ጥሪት ማፍራት መቻላቸውን ተናግረዋል ።
«ማህበራዊ ተሳትፎ ከህብረት ስራ ማህበራት መርሆዎች መካከል አንዱ በመሆኑ ይህንን ለሰላም ግንባታ ማዋል ይጠበቃል» ያሉት ደግሞ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገብረእግዚአብሄር ገብረዮሀንስ፤ የህብረት ስራ ማህበራት ዜጎች እርስ በእርስ እንዲደጋገፉና አብረው በመስራት እንዲያድጉ የሚያስችሉ በመሆኑ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የህዝቦችን አንድነት ያዳብራሉ ብለዋል።
ማህበራቱ የከተማና የገጠር ነዋሪዎችን ትስስርንም የሚያጠናክሩ በመሆናቸው ለህዝቦች መቻቻልና ለሀገር ሰላም ግንባታ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የህብረት ስራ ጽንሰ ሀሳብን ለዜጎች ማስተማር አደረጃጀቱንም በእኩል ማልማትና የማስፈጸም አቅምንም በማሳደግ እንደ ሀገር አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት የተጀመረውን ስራ ማፋጠን እንደሚጠበቅ አብራርተዋል።
በሲምፖዚየሙ « የህብረት ስራ ማህበራት ግብይት ለሰላም ግንባታ» በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን ከጥር 28 እስከ የካቲት አራት በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ እንደሚቆይም ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ