አዲስ አበባ፡- የግብርናው ዘርፍ ብዙ እድ ገት ማስመዝገብ ቢችልም አሁንም ማነቆዎች እንደበዙ በት ተገለፀ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ትናንት በተዘጋጀው ‹‹አዲስ ወግ፣ አንድ ጉዳይ›› የግብርናው ዘርፍ ቁልፍ የሪፎርም አጀንዳዎች በሚል በተካሄደው ውይይት የግብርናው ዘርፍ እድገት ቢመዘገብበትም አሁንም ማነቆዎች መብዛታቸው ተገልጿል።
በግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት የፖሊሲ አማካሪ ዶክተር አንተነህ ግርማ በውይይቱ እንደተናገሩት፤ ከ20 ዓመታት በፊት ከ100 ሚሊዮን ኩንታል ያላለፈው የሰብል ምርት በዘንድሮው የምርት ዘመን ወደ 325 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ብሏል። ስንዴ ከ20 ዓመት በፊት በሄክታር 16 ኩንታል ይመረት እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር አንተነህ፤ በአሁኑ ወቅት ወደ 29 ኩንታል ከፍ ማድረግ ተችሏል፤ በቆሎም ከነበረበት 19 ኩንታል በሄክታር ወደ 42 ኩንታል ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
በተሰራው ሥራ በገጠር የአርሶ አደሩ ህይወት ላይ ለውጥ እያመጣ ነው ያሉት ዶክተር አንተነህ፤ ለዚህም የገጠር የድህነት ምጣኔ በ1988 ዓ.ም ከነበረበት 47 ነጥብ 5 በመቶ በ2008 ዓ.ም ወደ 25ነጥብ 6 በመቶ መቀነሱን በማሳያነት አቅርበዋል። እነዚህ እድገቶች በአብዛኛው የተመዘገቡት በመንግሥት የልማት ሥራዎች ማለትም ከግብርና ምርምርና ኤክስቴንሽን ተቋማት፣ ከህብረት ስራ ማህበራትና ከአጋር አካላት ጋር በከፍተኛ ርብርቦሽ በተሰሩ ስራዎች መሆኑን አመልክተዋል።
የወጪ ንግዱን ከማሳደግ፣ ምርታማነትን ከማሻሻል፣ አዳዲስ የግብርና ምርቶችን ከማቅረብ፣ በገጠር የሥራ እድልን ከመፍጠር፣ ግብርናን ከማዘመንና ከአየር ንብረት ጋር የተስማማ ኢኮኖሚ ከመገንባት አንፃር ዘርፉ ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላት ተደርጎ መሰራቱን ዶክተር አንተነህ ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስቴር ስምንት ያህል የዘርፉ ማነቆዎችን መለየቱን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ውስጥ ያልዘመነ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ የቴክኖሎጂ ግብዐቶች ቀጣይ አለመሆን፣ ያልዘመነ የምርት ግብይት ስርዓት፣ የመስኖ አውታሮች አለመስፋፋት፣ የግሉን ዘርፍ የሚያበረታታ ስርዓት አለመዘርጋት የሚሉትና ሌሎችንም ለይቶ እንዳቀረበ ገልጸዋል።
የዘርፉን ችግሮች ለይቶ ለመተንተን እና የአፈፃፀም ስልት ለማዘጋጀት የማስፈፀም አቅም ውስንነት እንደተስተዋለ የገለፁት ዶክተር አንተነህ፤ የግብርና መዋቅራዊ ሽግግሩ የዘገየ መሆኑን በማንሳት መንግሥት ችግሮችን ለብቻው መፍታት እንደማይችል በማመኑ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያሻግር ግብርና ለመፍጠር ሪፎርም ቀርፆ የግሉ ዘርፍ አስተዋፅዖ ላይ ትኩረት ለማድረግ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም በመድረኩ ተነግሯል።
የእንስሳት ሀብት ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ወርቅነህ አያሌው ፤በግብርናው ዘርፍ የወተት ሀብት ልማት፣ የስጋና እንቁላል ልማት፣ የመኖና ንብ ልማት ስራዎች ላይ መንግሥት በማሻሻያው በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የግብርና ኢኮኖሚስት የሆኑት ፕሮፌሰር አለማየሁ ስዩም በበኩላቸው፤ ለድርቅ የመጋለጥ ስጋትን እየጨመረ ያለውና ከአፈር መሸርሸር ጋር ተያይዞ የሚከሰተው መሬት መራቆት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፀው፣ የአርሶአደሩ የመሬት ይዞታ አናሳ መሆን ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሆራይዘን ፕላንቴሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አህመድ፤ መንግሥት በአነስተኛ መሬት ላይ ሰፊ ምርት ማምረትን በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስበው፤የግሉ ዘርፍ የተሰሚነት ማጣት፣ የግንዛቤ ችግር እና አላስፈላጊ ቁጥጥር እየተደረገበት ስለሆነ ይህ ሊቀረፍ ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ የተገኙ ሀሳቦችም ለፖሊሲና ማሻሻያዎች በግብዓትነት እንደሚያገለግሉ የገለፀው የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ‹‹አዲስ ወግ፣ አንድ ጉዳይ››፤የሀሳብ ልዩነቶችን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት መደማመጥና ጉዳዮችን በንግግር መፍታትን አላማው አድርጎ እየተከናወነ ስለመሆኑ ገልጿል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች አንዱ የግብርናው ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2012
ድልነሳ ምንውየለት
ፎቶ፡- ዳኜ አበራ