- ሠራዊቱ ከትግራይ እንዳይወጣ የሞከሩት ህዝቡና የክልሉ መንግሥት አይደሉም
- መከላከያን ከኃላፊነቱ ውጪ የክልሎችና የፖለቲካ ሥራን የማሠራት ፍላጎት አለ
- በሠራዊቱ ላይ ጥላቻ በመንዛት አገርን ለማፍረስ የሚሠሩ አሉ
አዲስ አበባ፡- የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) በሬ አርዶ እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ በተቀበለው ህዝብ ላይ አሰቃቂ ድርጊት መፈጸሙን፣ ሠራዊቱ ከትግራይ ክልል ሲንቀሳቀስ እንዳይወጣ ወጣቶች መሬት ላይ እንዲተኙ ያደረገው ህዝቡና የትግራይ ክልል መንግሥት አለመሆናቸውን፣ የክልሎችና የፖለቲካኞችን ሥራ መካላከያ እንዲሠራ የመፈለግ አዝማሚያ መኖሩንና ሠራዊቱ ላይ ጥላቻ በመንዛት አገሪቱን ለማፍረስ የሚሠሩ ኃይሎች መኖራቸውን ተናገሩ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት በ17ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የ2011 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻፀም ሪፖርትን አዳምጧል፡፡ በዚህም ወቅት የምክር ቤቱ አባላት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት ለምን መግባት አልቻላችሁም? ችግሩ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? በአንዳንድ ቦታዎች ሠራዊቱ እንዳይንቀሳቀስ የማገት ተግባር ይታያል፡፡ በትብብር ትሠራላችሁ ወይ? በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት የቅድመ መከላከል ሥራ በመሥራት ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ስለምን ማቆም አልቻላችሁም? ተቋሙን ከሙስና ነፃ ለማድረግ ምን ያህል እየሠራችሁ ነው? ከኮንትሮባንድ ጋር በተያያዘ የተቋሙ ኃላፊዎች ላይ የሚነሳ ሀሜት አለና ምን ዕርምጃ ወሰዳችሁ ሲሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡
የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የዘመቻ መመሪያ ኃላፊ ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ በሰጡት ምላሽ በአገሪቱ ምዕራብ ክፍል የተፈጠረው ችግር የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) በመጀመሪያ ህዝቡ በሬ፣ በግና ዶሮ አርዶ ተቀበላቸው፡፡ ደረጃ በደረጃ ህዝቡን ወደ መዝረፍ ገቡ፡፡ በመቀጠልም በሬ አርዶ በተቀበላቸው ህዝብ ላይ አሰቃቂ ድርጊት ፈጸሙ፡፡ በመጀመሪያ መንግሥት አትንኳቸው በማለቱ መከላከያ ሠራዊት አልገባም፡፡ ሠራዊቱ በመንግሥት ታዞ ከገባ ቅርብ ጊዜ ሲሆን በሦስት ሳምንታትም በአካባቢው ለውጥ አምጥቷል፡፡ በድርጊቱ የተሳተፉት አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ የአገር ሽማግሌዎችን ጭምር በመጠቀም ከድርጊታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ዋናዎቹና የግጭት ኪራይ ሰብሳቢዎች ግን እየተመቱ ነው ያሉት ኤታማዦር ሹሙ የመከላከያ ሠራዊትን ልብስ ለብሰው ህዝብን እየገደሉ በመጣልም ሠራዊቱን የማስጠላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
‹‹ሠራዊቱ ከትግራይ ክልል ሊወጣ ሲል እንዳይወጣ ታግቷል›› ስለተባለውም ጀኔራል ብርሃኑ በሰጡት ምላሽ ሠራዊቱ የትግራይ ህዝብም ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ የእራሱን ወታደር አያግትም፡፡ ህዝቡ ፈርቻለሁ አትሄዱብን ሲልም ፍርሐቱ እስኪቀረፍ ጥሎ አይሄድም፡፡
በጸጥታ በኩል በትግራይ ክልል ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም፡፡ በጎረቤትም ሆነ በአካባቢውም መረጃ ያለው እኛ ጋር ነው፡፡ ለመንግሥትም መረጃ የምንሰጠው እኛ ነን፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ግን የትግራይን ህዝብ በማስፈራራት ሰይፍ እየሳሉ የሚኖሩ ጥቂት ነጋዴዎች አሉ፡፡ እነዚህን ነጋዴዎች ህዝቡ በቅርቡ ያውቃቸውል፡፡ ይህ ተግባርም የትግራይ ክልል ህዝብና መንግሥት ተግባርም አይደለም ብለዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ ከውጭ ወራሪና በአገር ውስጥ በትጥቅ ትግል መንግሥትን ለመቀየር የሚደረግን ሙከራ መከላከል፣ የተፈጥሮ አደጋ ሲከስት እገዛ ማድረግና ከክልሎች አቅም በላይ ሲሆን በክልሎች ጥያቄ መሰረት ግጭቶችን ማክሽፍ ቢሆንም በክልሎች፣ በፖለቲካ ኃይሎችና በሌሎች የጸጥታ መዋቅር ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች መከላካያ እንዲሠራ የመፈለግ ሁኔታ አለ፡፡
ይህ ተገቢነት የሌለውና የመከላከያ አቅምን የሚያዳክም ነው፡፡ በአዋጅ ከተሰጠው ኃላፊነት ውጪ የአገር ውስጥ የደህነነት ስጋቶችን መሰረት አድርጎ መከላከያ አይደራጅም፡፡ በአዋጅ የተሰጡትን ኃላፊነቶች መወጣትን መሰረት አድርጎ ስለሚደራጅ ሌሎችም መሠራት የሚገባቸውን ሥራዎች መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡ ይሁንና ማገዝ የሚገባው ነገር ሲኖር ግን ያግዛል ብለዋል፡፡
መከላከያ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ፤ ሁሉንም ህዝቦች የሚያሳትፍና የአገሪቱን ጥቅም የሚያስከብር የታጠቀ ኃይል ለመሆን ሪፎርም እያካሄደ ነው፡፡ በመከላከያ ውስጥ የተሠራው ሪፎርም የአገሪቱን የስጋት ሁኔታ በመተንተን፣ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጣቸውን መርሆዎችና የሠራዊቱን ተልዕኮ መነሻ በማድረግ ያሉንና የጎደሉንን በመለየት ለመሰልጠን፣ ለመታጠቅ፣ የሚሰጥ ግዳጅን በሙሉ አቅም ለመወጣት በሚያስችል ደረጃ ነው፡፡
የሠራዊት ማቋቋሚያ አዋጅን አሻሽሏል፡፡ የሙያ ግንባታ እያካሄደ ነው፡፡ አደረጃጀቱንም በአዲስ ቀይሯል፡፡ በዚህም ወታደርነት ተመራጭ የሥራ መስክ እንዲሆን በሪፎርሙ አስቀምጧል፡፡ የበጀት አያይዝን ግልጽ በማድረግ ከሙስናና ማጭበርበር እንዲጸዳና ዴሞክራሲያዊ ተቋም ለማድረግም የኦዲት ስርዓቱ እንዲስተካካል በአዋጁ ላይ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡
ወታደር ለአገሩ ታማኝና አገልጋይ እንዲሆን ህዝቡ ‹‹የእኔ ነው የሚል አስተሳሰብ መፍጠር አለበት›› አሁን ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ሠራዊቱ ድክመት ቢኖርበትም አንኳ የመንግሥትና የህዝብ ድክመት ነው፡፡ ሠራዊቱን መቀጥቀጥ መሪዎቹን ማብጠልጠል ይታያል፡፡ የፖለቲካ አመራሩም ሆነ ህዝቡ ይህንን መታገል አለበት፡፡ እኛ በሙያችን የምናገለግል የአገሪቱ የመጨረሻ ምሽግ መሆናችንንም መገንዘብ አለበት ብለዋል፡፡
ተቋሙ የሚፈርስ የሚመስላቸው ጋዜጠኞችና የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች ፤ ሠራዊቱን በጀምላ ሌባ ነው ይላሉ፡፡ ችግር በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች እንዳለው ሁሉ በመከላከያም ሊኖር ይችላል፡፡ ይሁንና ሁሉ ነገሩን ሰጥቶ በእውነት አገሩን የሚያገለግለውን አብዛኛውን ሠራዊት አንድ ላይ ጨፍልቆ ሌባ ማለት ግን አገርን ያፈርሳል ሲሉ ነው ያስጠነቀቁት፡፡
ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ስህተቶችን ተቋሙ እያስተካከለ ነው ያሉት ጀኔራሉ የተፈጠሩት ችግሮችም የግለሰቦች እንጂ የተቋሙ አይደሉም፡፡ ሠራዊቱ ለአገሩ የመጨረሻ ዘብ መሆኑንም መሪ ሳይኖር ለ45 ቀናት በመምራትና ሥርዓት እንዲቀጥል በማድረግ አስመስክሯል፡፡ ወታደሩ ተራ ሚሊሽያ ቢሆን ኖሮ እንደዚያ አይሆንም ነበር ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ሠራዊቱ እንዲፈርስ የሚደረግ ዘመቻ አለ፡፡ ሠራዊቱን አቅም የሌለው፤ በብሄር የሚባላና ጭራቅ አድርጎ የመሳል ሁኔታም ይታያል፡፡ ሠራዊቱ ከፈረሰ አገር ይፈርሳል በማለት የመሥራት ሁኔታ አለ፡፡ ተቋሙ እንደ ተቋም የሚሠራው እንዳለ ሆኖ ይህን ዘመቻ ለመግታት ምክር ቤቱም የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡
የምህረት አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ የኩብለላ ወንጀል ፈጽመው በምሕረት አዋጁ ተጠቃሚ ለመሆን ከ41 ሺህ በላይ ኮብላዮች ተመዝግበው የምህረት የምስክር ወረቀታቸውን በመውሰድ ላይ ሲሆኑ ምዘገባው አሁንም እንደቀጠለ ነው ሲሉም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ገልጸዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድም ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የኦዲት ግልጽነት ለመፍጠር የህግ ማሻሻያ መደረጉን፣ ለመከላከያ ተጠሪ የሆኑ ተቋማትን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነና አሁን ያሉት አምስት ሴት ጀኔራሎች ብቻ ቢሆኑም በቀጣይ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ በመከላከያ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ተግባራት አመርቂ መሆኑን ገልጾ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያንቀሳቅሱት ተጠሪ ተቋማት አፈጻጸም እንዲሻሻልና በሪፖርቱ እንዲካተት እንዲሁም የኦዲት ግኝቶችን እየተከታተሉ ማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ ላይ በትኩረት እንዲሠራ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
አዲስ ዘመን ጥር 1/2011
በአጎናፍር ገዛኽኝ