አዲስ አበባ፦ ለአራት የመንግስት መስሪያ ቤት ሴት ሰራተኞች የማህጸን ጫፍና የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ሊያደርግ መሆኑን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ አስታወቀ።
የኮሌጁ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንዋይ ጸጋዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለመጀመሪያ ጊዜ በአራት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ለሚያገለግሉ ሴት ሰራተኞች ቅድመ ምርመራውን ለመስጠትና ችግሩ ለሚገኝባቸውም ሴት ሰራተኞች የተለያዩ የህክምና ድጋፎችን እንዲያገኙ ለማድረግ ወስኗል።
‹‹የጥር ወር የእናቶች ጤናማነት ወር እንደመሆኑ ምርመራውን መስጠት አስፈልጓል።›› ያሉት አቶ ነዋይ፣ የመንግስት ሰራተኞች ካለባቸው ተደራራቢ ኃላፊነት የተነሳ በየጊዜው ወደ ጤና ተቋማት እየሄዱ ምርመራዎችን ለማድረግ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ ሆስፒታሉም አገልግሎቱን በአቅራቢያቸው አግኝተው ራሳቸውን ማወቅ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል።
በየተቋማቱ የህክምና ቡድኖች እንደሚላኩ ተናግረው፤ በዚህም ሴቶቹ የማህጸን ጫፍ እንዲሁም የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ የሚያደርጉበትን ሁኔታ በመፍጠር ያሉበትን የጤና ሁኔታ የመለየት ስራ እንደሚከናወን አቶ ንዋይ አስገንዝበዋል፡፡ ከምርመራው በኋላም ችግሩ የተገኘባቸው ሴቶች ተጨማሪ የህክምና ክትትል በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እንዲያገኙ እንደሚደረግም አመልክተዋል።
ለዚህም ከየተቋማቱ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጋር በመሆን የተከናወነው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ሰራተኞቹ በሙሉ ፍቃደኝነት ምርመራው ራሴን ለማወቅ ያስፈልገኛል ብለው እንዲያምኑና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።
እንደ አቶ ነዋይ ማብራሪያ፤ ተቋማቱ የተመረጡበት ዋናው መስፈርት ብዙ ሴት ሰራተኞችን የያዙ በመሆናቸው ነው። ይህ የሙከራ ትግበራ እንደመሆኑ በቀጣይ ወደ ሌሎች ተቋማት በመሄድ አገልግሎቱን ሰፋ አድርጎ ለመስጠት ሆስፒታሉ አቅዷል።
ከጥር 2 እስከ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደው የማህጸን ጫፍ እና የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የባህልና ቱሪዘም ሚኒስቴር ሴት ሰራተኞች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡በአንድ ተቋም ለሁለት ቀናት በሚሰጠው ምርመራ በርካታ ሴቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ከዚህ ቀደም በመድሀኒአለም ትምህርት ቤት ፣ በሰላም ክሊኒክ፣ በጃንሜዳ ጤና ጣቢያና በሌሎች የክልል ከተሞች ተመሳሳይ የቅድመ ካንሰር ምርመራዎችን ማከናወኑን ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2011
በእፀገነት አክሊሉ