አዲስ አበባ ፡- ‹‹ሰላም ዋናው ትኩረታችን ነው ፡፡›› ሲሉ የሽግግር አካል ኦነግ ሊቀመንበር አቶ ገላሳ ዲልቦ አስታወቁ፡፡ ለውጡ በመልካም መንገድ ላይ ነው የሚል እምነት እንዳላቸውም ገለጹ፡፡
ሊቀመንበሩ አቶ ገላሳ ዲልቦ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤በሀገሪቱ ችግሮች ቢስተዋሉም፤ የሚታይ ለውጥም አለ፡፡ ችግሩን ደግሞ ታግሎ መፍታት ይቻላል፡፡
‹‹ህዝቡ ምን ይዛችሁ መጣችሁ የሚለን ከሆነ የህዝቡ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ አንዱ ዋና ትኩረታችን ሰላም መሆኑን እገልጻለሁ፡፡ ሲሉ ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡
በውጭ ሀገር እያሉ ‹‹በአገሪቱ የሰላም ነፋስ መንፈስ አለበት፤ ይህ ለውጥም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቀጠል አለበት›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር በጥልቀት የተጀመረውን ለውጥ እንዲቃኙና ድጋፍም እንዲያደርጉ እንዳነሳሳቸው አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት ድርጅታቸው በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ በወቅቱ በመደገፍ መግለጫ ማውጣቱንም ጠቅሰዋል፡፡
ድርጅታቸው ወደ አገሪቱ በመመለስ በተጀመረው ለውጥ ውስጥ መሳተፍ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከመንግስት ጋር ለመወያየት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረው፣ በጀርመን በርሊን ከተማ ከእነ አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ እንዲሁም በኢፌዴሬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከተመራው ልዑክ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ .
‹‹ዴሞክራሲያዊ ስርአትን መገንባት ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡የዴሞክራሲ ተቋማትን በእጅጉ ይፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲን ለመገንባት በራሱ ትልቅ ስራ ይጠይቃል፡፡›› ያሉት አቶ ገላሳ ፣ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በመጀመሪያ ደረጃ ለሰላም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህን ስንል ደግሞ ለሰላም እንታገላለን ማለት ነው፡፡››ብለዋል፡፡
ሊቀመንበሩ ‹‹ለውጡ በመልካም መንገድ ላይ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡››ሲሉም ተናግረዋል፡፡ለውጥ ሁሌም በፈተና ውስጥ አልፎ እንደሚመጣ ጠቅሰው፣ሁሌም ቢሆን ዋጋ እንደሚያስከፍል መዘንጋት እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡
‹‹በለውጥ ውስጥም ተግዳሮት እንዳለ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ለውጡ ስኬታማ ይሆን ዘንድ መንግስትም አንዳንድ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል፡፡››ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በለውጡ ባልተደሰቱ ሰዎች ሳቢያ ለውጡ ከመጣ አንስቶ አገሪቱ መረጋጋት እንደማይታይባት ተናግረዋል፡፡ በለውጡ ያልተደሰቱት ወገኖች አሁን ያለው መንግስት ደካማ መሆኑን እንደሚገልጹ አመልክተው፣ ለውጡን አቅሎ ማየት እንደማይገባ ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡ ለውጡን አጠናክሮ በመቀጠል ስጋትን ማስወገድ እንደሚቻልም አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2011
በአስቴር ኤልያስ