-መረጃ በመከልከል የተጠመዱ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል
– ለሃይማኖት ተቋማት ጥያቄም መንግስት ምላሽ መስጠት አለበት አለ
አዲስ አበባ፡- መረጃን በመከልከልና ተባባሪ ባለመሆን የተጠመዱ የመንግሥት አካላት ከድርጊታ ቸው ሊታቀቡና አሠራራቸውን ሊያስተካክሉ እንደሚገባ የኢፌዴሪ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ። የሃይማኖት ተቋማትንና አማኞችን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን አስመልክቶ ተቋማቱ ለመንግሥት ላቀረቡት ጥያቄም መንግሥት ዘላቂ መፍትሄ ሊፈልግ እንደሚገባም አስገንዝቧል።
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ትናንት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ መገናኛ ብዙኃን የሚሰሩትን ዘገባ ሚዛናዊ ለማድረግ የፌዴራልንም ሆነ የክልል መንግሥት ኃላፊዎች መረጃ ሲጠይቁ ተባባሪ ያልሆኑ አካላት ታይተዋል።
ለአብነት የትግራይ ብ/ክ/መ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በክልሉ ባሉ የወረዳ እና የዞን ጥያቄዎችን በተመለከተ፤ የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ ቤት ለኅብረተሰቡ የሚያከፈፍልበትን ሥርዓት አስመልክቶ፤ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ስለታገቱ ተማሪዎች መረጃ እንዲሰጡ ተጠይቀው ተባባሪ ካልሆኑት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጿል። ስለሆነም በስም የተጠቀሱት ተቋማትም ሆኑ ሌሎች መረጃ በመከልከልና ለመስጠት ተባባሪ ባለመሆን የተጠመዱ የመንግሥት አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡና አሠራራቸውን ሊያስተካክሉ ይገባል።
ተቋሙ በመግለጫው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋማትንና አማኞችን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መከሰታቸውን ጠቅሶ፣ ‹‹ይህንንም መሠረት አድርገው የሃይማኖት ተቋማቱ ከደህንነት፣ ከዋስትና፣ ከሕግ የበላይነትና ከተጠያቂነት ጋር የተያያዙ ለመንግሥት ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ቢኖሩም ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘታቸው ጥቃቶቹ አሁንም እየተከሰቱ ይገኛሉ።›› ሲል አብራርቷል።
በቀጣይም ስለሚፈጠሩ ችግሮች ዋስትና የሚሰጥ ነገር እንደሌለም አመልክቷል። ይህም በሃይማኖት ተቋማቱና ተከታዮቻቸው ዘንድ ትልቅ ቅሬታና ስጋት መፍጠሩን አስገንዝቦ፣ መንግሥት ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለችግሮቹ ደግሞ ዘላቂ መፍትሔ ይፈልግ ሲል ጥሪውን አስተላልፏል።
ከዚህም በተጨማሪ ከመሠረተ ልማት ዝርጋታ ጋር ተያይዞ በወረዳዎች በማን አለብኝነት ነጠላ ዋጋን አጋንኖ የማቅረብና ካሳ የማይገባቸው ንብረቶችን አካቶ የማቅረብ አድሏዊ አሠራሮች እንዲስተካከሉና የታገቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመልክቶ መንግሥት መረጃ በመስጠትም ሆነ ችግሩን በመፍታት ረገድ የተፋጠነ ምላሽ እንዲሰጥ ተቋሙ በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳስቧል።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2012