አዲስ አበባ፡- የባህል መገለጫ የሆኑ የባህል አልባሳት አምራቾችን የግብአት ችግር ለመፍታት የመንግሥት ተቋማት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አስታወቁ። አምራቾቹ ተደራጅተው ግብአቶቹንም ሊያስመጡ በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ውይይት እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዕደ ጥበብ ማበልፀግ ገበያ ሥራዎች ዳይሬክቶሬት አስተባባሪው አቶ ነጋሽ አሰፋ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ ከማኅበራት፣ ከዲዛይነሮች፣ ከሸማኔዎችና ንግድ ሚኒስቴር ጋር ከሁለት ወር በፊት በተካሄደ የውይይት መድረክ የግብአት ችግር ጉዳይ ተነስቷል።
ዲዛይነሩ እና የሙያ ማኅበራቱ ተደራጅተው ከመንግሥት ጋር ተነጋግረው ግብአቱን ከውጭ ማስገባት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል፤ እነዚህ አካላት እንዴት እንደሚደራጁና መደራጀታቸው ምን ዓይነት ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል በሚለው ላይ እየተሰራ ነው።
አስተባባሪው ክሮችን ከውጭ የማስገባቱ ሥራ በጥቂት ሰዎች እጅ የተያዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህ አስመጪዎች ዋጋውን እንደ ፈለጋቸው እንደሚጨምሩና ገዢዎችም የመወዳደር አቅማቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህም የባህል አልባሳትን ኅብረተሰቡ እንዳይጠቀም ጫና እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ከንግድ ሚኒስቴርም ጋር በዚህ ዙሪያ ስትራቴጂ (ስልት) ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን አቶ ነጋሽ ጠቅሰው፣ መፍትሄው ሸማኔውና ነጋዴዎች በሠፊው ግብአቱን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኙበት ገዢውም መደራደር የሚችልበትን መንገድ መዘርጋት መሆኑን ገልጸዋል።
የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዳይሬክተር አቶ ስዩም ጅራ በበኩላቸው በሀገር ውስጥ እንደ ባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ ያሉ ፋብሪካዎች ግብአቶችን እንደሚያመርቱ ጠቁመው፣ አምራቾቹም ተደራጅተው ክሮቹን ሊያስመጡ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ አስታውቀወዋል። ለእዚህም አምራቾቹን በመሰብሰብ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መሪ ወይዘሮ አቦዘነች ነጋሽ ከሀገር ውስጥ ግብዓት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በከፍተኛ መጠን ያመርቱ እንደነበርና አሁን ግን መዳከማቸውን ተናግረዋል።
«ፋብሪካዎቹ የሚሸጡበት ዋጋ ከፍተኛ ነው፣ የእኛ ጥቃቅኖች ደግሞ የመግዛት አቅም የላቸውም።»
ያሉት ወይዘሮ አቦዘነች፣ ስለዚህ ሸማኔዎቹ በሚችሉት አቅም በችርቻሮም ባይሆን በተወሰነ መልኩ ተደራጅተው ግብአቱን ከፋብሪካዎቹ እንዲወስዱ ለማድረግ የጋራ መድረኮች እያዘጋጀን ሥራ ስንሠራ ቆይተናል ብለዋል።
ፋብሪካዎቹም ገበያውን የመቋቋም ችግር እያጋጠማቸው መምጣቱን ጠቅሰው፣ በተፈለገው መጠን ግብአቱን ለጥበብ አምራቾቹ ሊያደርሱ እንዳልቻሉም ተናግረዋል። «እንዲያም ሆኖ ፋብሪካዎቹ ከገበያ አልወጡም፤ እየሠሩ ናቸው፤ እንደ ዜግነትም ኃላፊነት እና ግዴታ አለባቸው፤ እኛም ጥረታችንን እንቀጥላለን» ሲሉ አብራርተዋል።
ወይዘሮ አቦዘነች እንዳሉት፤ ኢንተርፕራይዞች ራሳቸውን እያጠናከሩ ቶሎ ቶሎ የገበያ ዕድል እየተፈጠረላቸው ከሚፈለገው ገበያ ጋር ራሳቸውን እንዲያሳድጉ የገበያ አማራጮችን ማስፋት የግብአቶችን ዋጋ ተቋቁመው እንዲገዙ ማድረግ እና ግብአት ከሚያመርቱ ፋብሪካዎች ጋር በመተሳሰር ተደራጅተው ግብአቱን ከነሱ ማግኘት እንዲችሉ አማራጮችን በማቅረብ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ