አዲስ አበባ፡- በአርብቶ አደርና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ተመጣጣኝ ልማት ከማረጋገጥ አኳያ የሰላም ሚኒስቴር ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባው የግብርና አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የሰላም ሚኒስቴርን የ2012 በጀት ዓመት የስድስት ወር እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ትናንት ባደመጠበት ወቅት ከቋሚ ኮሚቴ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው በሚኒስቴሩ አመራሮች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ተወካይ አቶ ነጋልኝ ዮሴፍ እንደገለፁት፤ በአርብቶ አደርና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ተመጣጣኝ ልማት ከማረጋገጥና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ያልተጠናቀቁ ነባር ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅም ሆነ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመፈፀም በኩል ክፍተት ታይቷል፡፡ የታየውም አፈፃፀም ከቅድመ ዝግጅት የዘለለ ስላልሆነ በቀጣዮቹ ጊዜያት የተሻለ ስኬት እንዲኖር የተጠናከረ ርብርበር ማድረግ ይገባል፡፡
ድርቅ የሚያስከትለውን አደጋ ከመከላከል አኳያ የሚከናወኑ ተግባራት ድጋፍ በሚሹ ክልሎች የሕልውና ጉዳዮችም ጭምር መሆናቸውን ገልጸው፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከርና የተሻሉ ስልቶችን መንደፍ ተጠቃሽ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አርብቶ አደሩን ኅብረተሰብ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠቃሚ የማድረግ ጉዳይ ወደልማት ማዕከላት እንዲሰባሰብ ከማድረግ ሥራ ጋር በጥብቅ የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአንድ ክልል የሚጀመረው ሌላው ክልል ላይ የሚተው ከመሆን ወጥቶ ተቀራራቢ አፈፃፀም እንዲኖር መስራት ትኩረት የሚሰጠው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በነባር የመንደር ማሰባሰቢያ ማዕከላት የመሠረተ ልማት የማሟላት ሥራውም የርብርብ ማዕከል መሆን እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አፅንዖት እንደሰጠው ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ነጋልኝ ገለፃ፤ በእጥረት ከተነሱት ጉዳዮች መካከል 5ሺህ 500 ግንባር ቀደም አርብቶ አደሮችን በሥራና ቁጠባ ባህል ዙሪያ የማህበረሰብ ውይይት በማድረግ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ቢታቀድም በጋምቤላ ክልል ብቻ ከመሰልጠናቸው ውጪ ሌሎች ክልሎች ላይ አለመከናወኑ ተጠቃሽ ነው፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በጠንካራ ጎኑ ካያቸው ሥራዎች መካከል በዘመናዊ የመንደር መፍጠሪያ ማኑዋል ላይ በየደረጃው ለሚገኙ ወደ 200 አመራርና ባለሙያዎች አቅማቸውን እንዲገነቡ ለማስቻል የተሰራው ሥራ ይጠቀሳል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የፀደቀውን 450 ሚሊዮን ዶላርም በፕሮግራሙ በታቀፉ መቶ አርብቶ አደር ወረዳዎች ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉና ኅብረተሰቡ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሰራታቸው በጥንካሬ መወሰዳቸውን አቶ ነጋልኝ አብራርተዋል፡፡
ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የሚኒስቴሩ የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በቋሚ ኮሚቴው የተነሱ የሰው ኃይል እጥረት፣ የቅንጅት ችግር፣ የቦርዱ ጊዜ ማጣትና ሌሎችም ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸውና በግብዓትነትም የሚወሰዱ ናቸው፡፡ የቅንጅትና የቁርጠኝነት ችግሩን ለማስተካከል ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር የሚሰራ ይሆናል፡፡ ፖሊሲው ከፀደቀ በርካታ ሥራ ለመስራት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ሪፖርቱን ያቀረቡት የሚኒስቴሩ የፌዴራሊዝምና ልዩ ድጋፍ ዳይሬክተር ጀነራል ፕሮፌሰር ደገፋ ቶሎሳ እንደገለፁት፤ በነባር የመንደር ማሰባሰብ ማዕከላት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲሁም የሥራና ቁጠባ ባህልን በማሻሻል ላይ ሥራዎች ተሰርዋል፡፡ በአግባቡ ሥራዎችን ለመስራት ግን የአርብቶ አደር ፖሊሲ ፀድቆ ወደሥራ መግባት አለመቻሉ ማነቆ ሆኗል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 19/2012
አስቴር ኤልያስ