ካፒቴን ማርታ ጌታቸው የሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አሽከርካሪ ናት። በአሁኑ ወቅት በትራፊክ አደጋ በርካታ ሰዎች ከሚሞቱባቸው ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ በእጅጉ የሚያሳዝናት ካፒቴን ማርታ፣ ምንም እንኳን የአደጋዎቹ ምክንያት የተለያየ ቢሆንም፣ በአሽከርካሪዎች ቸልተኝነትና ብቃት ማነስ የሚከሰቱት አደጋዎችን መመለከት ግን በእጅጉ እንደሚያስቆጫት ትገልፃለች።
‹‹ሥራው በጣም ፈታኝ ነው፣ የአንድ ሰከንድ ስህተት በቅጽበት አስከፊ አደጋን ይፈጥራል.›› የምትለው ማርታ፣ ሺዎችን ከሞትና ከከፋ አደጋ ለመታደግ በተለይ ለብዙኃን አገልግሎት የሚሰጡ ካፒቴኖች ጠንቃቃና ‹ካሰቡበት ቦታ ለመድረስ እኔ እብስ እኔ እብስ ከመባባል ይልቅ ቅድሚያ መስጠት፣ ከሁሉ በላይ ትእግስት ሊኖራቸው የግድ ነው›› ትላለች።
ይህ እሳቤዋ ለተገልጋዮች ከአደጋ የፀዳ አገልግሎት እንድትሰጥ ሁነኛ ምክንያትና አቅም እንደሆናት የምትገልጸው ማርታ፣ የሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አደጋን ተከላክለው በማሽከር ልዩ እምርታ ላሳዩ የተቋሙ አውቶቡስ ካፒቴኖች ልዩ የእውቅና የሽልማት ፕሮግራም ትናንት ሲያዘጋጅ ተሸላሚ ካደረጋቸው መካከልም ግንባር ቀደም አድርጓታል።
ድርጅቱ ‹‹በከተማዋ የትራፊክ ደህንነት ላይ አስተዋፅኦ አበርክተሻል›› በሚል የእውቅና ሽልማት በማበርከቱ እጅግ ደስታ እንደተሰማትና ከሁሉ በላይ ከባድ ኃላፊነት እንደተረከበች የምትገልፀው ማርታ፣ መሰል መርህ ግብሮች በሌሎችም ተቋማት መለመድ እንዳለባቸው፣ ይህም አደጋን በመከላከል ረገድ ውጤታማ እርምጃ ለመራመድ እንደሚያችል ነው ያስገነዘበችው።
ድርጅቱ ጦር ኃይሎች በሚገኘው ጎልፍ ክለብ ባካሄደው የእውቅና የሽልማት ፕሮግራም ላይ እንደ ማርታ ሁሉ ተሸላሚ ካደረጋቸው ካፒቴኖች መካከል አንዱ ዘውዱ ወልዴም፣ የትራፊክ አደጋ ከምንም በላይ አምራች ዜጎቻችን እየቀጠፈ መሆኑ ሊያስደንግጠንና አሳሳቢ ሊሆንብን ይገባል›› ይላል።
ለሚሊዮኖች እልቂትና ንብረት ውድመት መንስዔ የሆነውን የትራፊክ አደጋ መከላከል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑንና በተለይ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ኃላፊነት ግዙፍ መሆኑን የሚያስገነዝበው ዘውዱ፣ አሽከርካሪዎችም የበርካቶች ሕይወት በእጃቸው እንደመሆኑ ጠንቃቃና ትእግስተኛ ሊሆኑ እንደሚገባ በማስገንዘብ የማርታን ሃሳብ ይጋራል።
የእውቅና ሽልማቱ ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ሥራውን በትጋት እንዲወጣና ሌሎች ተከታዮችን እንዲያፈራም አቅም እንደሚፈጥለት የገለፀው ዘውዱ፣ ሌሎች ተቋማትም እንደ ሸገር ጠንቃቃ አሽከርካሪዎችን ቢያበረታቱ አደጋን የመከላከሉ ተግባር ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ እገዛ እንደሚ ያደርግ ነው ያስገነዘበው።
በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የትራንስፖርት ፍላጎት በዘመናዊ መንገድ ምላሽ ለመስጠት ከሦስት ዓመት በፊት መቋቋሙን የሚገልጹት ደግሞ የሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎይቶኦም ኃይሉ ናቸው።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺ ዘጠኝ መቶ በላይ ሠራተኞች፣424 አውቶቡሶች፣ 49 የስምሪት መስመሮች በማካለል በቀን ከ245 ሺ በላይ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን ከቦታ ቦታ እያጓጓዘ ይገኛል።76 የተማሪ ትራንስፖርት መስመሮችን በማውጣት በቀን ከ4 ሺ በላይ ተማሪዎችን ዘመናዊ የሰርቪስ አገልግሎት እየሠጠ ነው።
«ድርጅቱ ዘመናዊ አሠራርን ተላብሶ ከዚህ ደረጃ ለመድረሱ የታታሪና ጠንካራ ሠራተኞቹ ሚና የላቀ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ጎይቶኦም፣ድርጅቱ አደጋን ተከላክለው በማሽከርከር ልዩ እምርታ ላሳዩ የተቋሙ አውቶቡስ ካፒቴኖች ልዩ የእውቅና የሽልማት ፕሮግራም ማዘጋጀቱም ይህን ለማስቀጠል መሆኑን ይጠቁማሉ። ተሸላሚዎቹ ሠራተኞችም ጥንካሬን በመውረስና አርአያ በመሆን ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ሥራቸውን በትጋት ሊወጡና ሌሎች ተከታዮችን ሊያፈሩ ይገባልም›› ነው ያሉት።
የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እንደስሟ ለመፍካት የምትደርገውን የእድገት ግስጋሴ ከሚደግፉ ዘርፎች አንዱና ዋነኛው የብዙኃን ትራንስፖርት ዘርፉ ነው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ዘርፉን ዘመናዊ በማድረግ ከሌሎች ከተሞች ተርታ ለማሰለፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊነትን ያነገበ አሠራር መተግበር በተለይ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን በመገንባት፣ ችግሮችን በመለየት ብዙኃን ትራንስፖርት ዘመናዊ የኅብረተሰብ ጉልበት እንዲሆን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ያብራሩት።
ድርጅቱ አሁን ካለበት ደረጃ በተሻለ መልኩ ውጤቱ ለኅብረተሰቡ በሚታይ መልኩ የመስራት አቅም ተጠቅሞ ለማገልገል እንቅፋቶች እንዳሉበት በተለይ አውቶቡስ ማደሪያ፣ የነዳጅ መቅጂያ የእጥበት አገልግሎት መስጫ ቦታዎች እየተፈታተኑት መሆኑን በመጠቆምም፣ ከተማ አስተዳደሩም ችግሮቹን ለመ ፍታት ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግሥቱ ማሩም፣ ድርጅቱ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ከማቃለል ባሻገር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከአደጋ የፀዳና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ ስለመሆኑ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
ድርጅቱ ከተለያዩ የትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር በጋራ ይሰራል፣ ይሁንና መሰል ካፒቴኖችን ለማበረታታት የእውቅና ሽልማት እንደሚሰራና ተቋማት እምብዛም እንደማይስተዋሉ የሚገልፁት አቶ መንግስቱ፣ «መሰል ሽልማት ሠራተኞች አንድ ዓይነት ስሜትን እንዲጋሩ ይበልጥ እንዲበረታቱና ተገልጋዮቻቸውን ከአደጋ የሚጠብቁ ካፒቴኖችን ቁጥር ከፍ የሚያደርግ አርአያነት ያለው ተግባር ነው›› ብለዋል።ሌሎች ተቋማትም ይህን ተግባር መከተል እንደሚገባቸው ሳያስገነዝቡም አላለፉም።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2012
ታምራት ተስፋዬ