እሁድ ህዳር 14 2012 ንጋት የምዕራብ ሸዋ ዞን ቁንጮዋ አምቦ አንድ መርዶ የሰማች ያህል ፀጥ ብላለች። ቀንዋን በሀዘን እንደምታሳልፍ ሹክ የተባለች ይመስል አኩርፋለች። በአስደናቂ ተፈጥሮ የተኳለው ውብ ገፅታዋን የሚያላብሳት ከምስራቃዊ ክፍልዋ የምትፈነጥቀው የዘወትር ፀሀይ ተደብቃታለች።
አምቦ ሀሳብ ገብቷት ውስጥዋ ስጋት ተፈጥሯል። ከተማዋ ተፈጥሮ ያደላት፤ ያለ ስስት በረከት የሞላባት ናትና ብዙው በጉያዋ አቅፋ ታሳድራለች። አቅምዋ በፈቀደው ያላትን በፍፁም ለጋስነት እየቸረች በእናትነት ካሳደገቻቸው ልጆችዋ መሀል የአብራኳ ክፋዮች ከሆኑት መካከል የ38 ዓመት ጎልማሳው አብዱልአዚዝ ጀማል አንዱ ነው።
ንጋት ላይ የሚያሳሱና ሁለት ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆቹና ሚስቱን ስሞ የቤተሰቡን ህልውና መሰረት የሆነውን ስራው ማከናወኛ ቁሳቁስ ገዝቶ ለመመለስ እንደሁልጊዜው አምቦን ለቆ ወደ አዲስ አበባ አቀና። ቀኑን አዲስ አበባ ውሎ፤ ያሻውን ሸምቶ ሰላም ያስገባው ዘንድ ለአምላኩ ተማፅኖውን አቅርቦ ወደ አምቦ በመጫን ላይ ያለ አንድ የህዝብ ማመላለሻ መኪና (ሀይሩፍ) ተሳፍሮ ጉዞ ወደ አምቦና ወደናፈቁት ልጆቹ ጀመረ።
ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ የሚወስደው መንገድ አንድ ነጭ ቀለም የተቀባ መለስተኛ ህዝብ ማመላለሻ (ሀይሩፍ) እንደ ንፋስ ሽው ይልበታል። እዚያ ውስጥ አብዱልአዚዝን ጨምሮ ለትምህርት ወደ አምቦ ዩኒቨርሲቲ የሚያመሩ ስድስት ተማሪዎች፣ አንድ የዩኒቨርሲቲው መምህርና ሌሎች ተሳፋሪዎችን ይዟል።
መዳረሻውን አምቦ ከተማ ለማድረግ በአራት እግሩ ሲሮጥ የነበረው መለስተኛ የህዝብ ማመላለሸ መኪና (ሀይሩፍ) ሆለታ ከተማ አቅራቢያ ከፊቱ ከሚመጣ ሲኖትራክ ገልባጭ መኪና ጋር ተላተመ። የምዕራብ ሸዋ ዞን ውብ ከተማ አምቦ ንጋት ያንዣበባት ስጋት ምሽት ላይ 18 ልጆችዋን የበላባት የመኪና አደጋ ስትሰማ አነባች። እሩቅ አልመው ወደፊት ይጓዙ የነበሩ ወጣቶች ከመንገድ ቀሩ። የበዙ ህልሞች በትራፊክ አደጋ መከኑ።
ተማሪ ስለእናት ተስፋዬ በትራፊክ አደጋው ህይወታቸው ካለፉት ወገኖች አንድዋ ናት። ወይዘሮ ሰብለ ወርቁ የተማሪ ስለናት ተስፋዬ አክስት ሲሆኑ በአደጋው ምክንያት በቤተሰቡ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት ሳግ በተናነቀው ድምፀት በአሳዛኝ መልኩ ይገልፁታል።
የአራተኛ አመት ተማሪ የነበረችው ስለእናት ለቤተሰቦችዋ ብቸኛ በትምህርት ውጤትዋም ስኬታማ ከሆኑት ተማሪዎች ትመደብ እንደነበረና በእርስዋ ህልፈት ምክንያት ወላጅ አባትዋ ስራ እስከማቆም መድረሱን የተማሪዋ አክስት ይገልፃሉ።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣው የመኪና አደጋ እያደረሰ ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል። በተለይ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የተመዘገበው የመኪና አደጋ ቁጥሩ ከፍተኛ መሆኑን የክልሉ ትራንስፖርት ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
አቶ ለማ ተፈራ በክልሉ ትራንስፖርት ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ናቸው። በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት በትራፊክ አደጋ ከፍተኛ ቁጥር መመዝገቡን ይናገራሉ። በዚህም የሞት አደጋ 829፣ ከባድ የአካል ጉዳት 766፣ ቀላል የአካል ጉዳት 926 እና 223 ሚሊዮን 320ሺ 380 ብር የሚገመት ንብረት በትራፊክ አደጋዎቹ መውደሙን ሪፖርቱን ዋቢ በማድረግ ያስረዳሉ።
በክልሉ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እየተሰሩ ባሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ለማ፤ ከችግሩ ስፋት አንፃር ግን የተጠናከረ ስራ እንደሚጠበቅ ያመላክታሉ። የትራፊክ አደጋው ለመቀነስ ባለስልጣኑ የቅድመ መከላከል ስራዎች እየሰራ መሆኑም ይገልፃሉ። የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች በተለያየ መገናኛ ብዙሀን በማስተላለፍ፣ አስጊ የሆኑ መንገዶች በመለየት ልዩ ቁጥጥር በማድረግ፣ የፍጥነት መቀነሻ (ብሬከር) በመስራት እና የትራፊክ ቁጥጥር በማድረግ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ባለስልጣኑ በቅርቡ የፍጥነት መቆጠጠሪያ መሳሪያ በመኪኖች ላይ ለመግጠም በዝግጅት ላይ መሆኑን የገለፁት አቶ ለማ፤ የመኪና አደጋን ለመቀነስ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት እቅድ መሆኑን ይናገራሉ።
ያለፉት 6 ወራት የትራፊክ አደጋን በሚያመ ላክተው ሪፖርት መሰረት በክልሉ በቀን በአማካይ የ5 ሰዎች ህይወት ያልፋል። ይህ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚዳርግ፤ ህልመኞች እንደወጡ የሚያስቀረው የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ባለ ድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የክልሉ ትራንስፖርት ባለስልጣን አሳስቧል።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2012
ተገኝ ብሩ