አዲስ አበባ:- በኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ ልማት ዘርፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠመ የመጣውን ችግር ለመፍታት መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም አካላት ትኩረት እንዲሰጠው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ አባተ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ ጥራት ያለውና ዓለም አውቆት ብራንድ የተሰጠው ቆዳ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ጥራትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ዘርፉ እየተቀዛቀዘ ከመምጣቱም በላይ ቆዳ በየቦታው እስከመጣል የተደረሰ በመሆኑ ይህንን ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል።
ኢትዮጵያ ውስጥ 80 ከመቶ የሚሆነው ቆዳ የሚገኘው ከበላተኛው ወይም ከየቤቱ ተሰብስቦ ሲሆን፤ ከቄራዎች የሚገኘው ቀሪው 20 በመቶው ብቻ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ ሁኔታ የሚሰበሰበው ቆዳ እንደሌሎች ሸቀጦች አንድ ቦታ የማይገኝና ከየቦታው ተሰብስቦ የሚመጣ መሆኑ ተናግረዋል።
‹‹50 በመቶ የጥራት ችግር እንስሳው በህይወት እያለ ጥሬ ቆዳው ላይ የሚፈጠር ሲሆን፤ ቀሪው የጥራት ችግር ደግሞ በእርድ ወቅት ይፈጠራል።›› ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት በተለይም የግብርናው ዘርፍ ለቁም እንስሳው ትኩረት በመስጠት ቢሰራ ቆዳ ሰብሳቢውም ሆነ ተረካቢው ሁሉም የየድርሻውን መወጣት ከቻለ ዘርፉ ውጤታማ የማይሆንበት ምክንያት አለመኖሩን አመልክተዋል።
ዘርፉ የተጋረጠበትን አደጋ ለመቀነስ መንግሥት በአሁን ወቅት ከፖሊሲ ጋር በተያያዘ አሉ የተባሉ ክፍተቶችን ለመድፈን በዘርፉ ተጥሎ የነበረውን 150 በመቶ ታክስ ሙሉ በሙሉ ማንሳቱን አስታውሰው፤ አሁን ቆዳን ከመጣል ወደ መሸጥ እየተመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ለቆዳ ሰብሳቢዎችም ሆነ ለተረካቢዎችና ለፋብሪካዎች መረጃውን በመስጠት እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ካሉ በኋላ፤ ይጣል የነበረው የበግ ቆዳ በአሁን ወቅት ከ40 እስከ 50 ብር መሸጥ ተጀምሯል ብለዋል።
ይሁን እንጂ፤ አሁን የተጀመረውን መነቃቃት ለማስቀጠል እና ይህን ትልቅ የአገር ሀብት ከብክነት ከመከላከል ባለፈ የጥራት ደረጃውን አሻሽሎ ከሀገር አልፎ በውጭ አገራት የኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ ተወዳዳሪ መሆን እንዲቻል ሁሉም በኃላፊነት ሊሰራ ይገባል በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሙ ኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ሰርጀቦ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የሚጠበቅበትን ያህል ገቢ እያስገኘ አይደለም ብለዋል።
ለዚህም ምክንያቱ ምርቱ ለሃገሪቱ ከሚያበረክተው ጥቅም አኳያ በልማቱ፣ በቁጥጥሩና በግብይቱ ረገድ የተሰጠው ትኩረት በቂ ባለመሆኑ ጋር ተያይዞ የምርቱ አዘገጃጀት እንዲሁም የግብይት ስርዓቱ ከወቅቱ የዓለም ገበያ ፍላጐት ጋር አብሮ መራመድ አልቻለም ብለዋል።
ጥራቱን በተመ ለከተም፤ እንስሳው በቁም እያለ ጥራቱ እንዲጠበቅ በባለቤትነት የሚመለከተው የግብርና ሚኒስቴር በመሆኑ የእንስሳው ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል።
ከዚህ በተጨማሪም በእርድ ወቅትም እንዲሁ ቄራዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለቆዳው ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው እንዲሁም በፋብሪካዎች አካባቢ በሚያጋጥመው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት የጥራት ደረጃው ወርዶ ለረዥም ዓመታት አገሪቷ ከዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት ሳትችል መቅረቷን ተናግረዋል።
ችግሩን ከመሰረቱ መፍታት ይገባል የሚሉት በግብርና ሚኒስቴር የስጋ ቆዳና ሌጦ ባለሙ ያ አቶ እዮብ አለሙ በበኩላቸው፤ በግብርናው ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ለእንስሳቱ የመኖ አቅርቦትን ማሻሻል እና የእንስሳት ህክምናን ተደራሽ ለማድረግ እና ለማስፋፋት የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተቀርፀው በርካታ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
‹‹ ይሁን እንጂ አጠቃላይ ያለው ችግር የጥራት ብቻ አይደለም። በአሁን ወቅት የሚታየውን የቆዳና ሌጦ ዋጋ ዜሮ የሚያስገባ እና ቆዳን እስከመጣል ደረጃ የሚያደርስ የጥራት ችግር የለም›› ይላሉ። አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ ችግር ሆኖ ዘርፉን የጎዳው የቆዳና ሌጦ ዋጋ መውረድ ነው። አንድ የፍየል ሌጦ ከአምስት ብር እስከ አስር ብር፤ የበግ ቆዳ ደግሞ ከ15 ብር እሰከ 20 ብር የሚሸጥ ሲሆን፤ የበሬ ቆዳ ደግሞ በኪሎ አምስት ብር እየተሸጠ እንዳለ ጠቁመዋል።
ይህ አሁን ያለው ዋጋ የሚያበረታታ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ቆዳ ሰብሳቢዎችም ሆኑ ተረካቢዎች ከስራው ወጥተዋል። በዚህም ምክንያት የተለያዩ ፋብሪካዎች ተዘግተዋል። ነገር ግን ከዚህ በፊት የነበረው የቆዳ ዋጋ ዘርፉን የሚያበረታታ ስለነበር ነጋዴዎች አሰባሳቢዎችን በማሰማራት ከቀበሌ እስከ ጎጥ ወርደው ቆዳ ይሰበስቡ ነበር።
አሁንም መንግሥት የችግሩን ስፋት ተመልክቶ መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይገባል ብለዋል።
የቆዳው ዘርፍ ያጋጠመው ችግር መሰረታዊና ውስብስብ እንደመሆኑ በገለልተኛ አካል ታይቶ ችግሩ ከምንጩ እንዲፈታ ሁሉም የበኩሉን ማድረግ እንደሚገባው ጠቁመው፤መንግሥት አሁን ካደረገው በከፊል ያለቀለትን ቆዳ ከቀረጥ ነፃ ከማድረግ ባለፈ ይህን በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለውን የቆዳ ዘርፍ ለማሻሻል ብሎም ወደ ቀድሞው ተፈላጊነቱ ለመመለስ በቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
ግብርና ሚኒስቴርም በበኩሉ የችግሩን ስፋት ሁሉም ህብረተሰብ በግልፅ እንዲያውቅ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በቅርቡ ዘጋቢ ፊልም ለመስራት ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ባለሙያው ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2012
ፍሬህይወት አወቀ