አዲስ አበባ:- በደብረብረሃን ከተማ የሚገኙ የኢንዱስትሪ መንደሮች የኤሌክትሪክ ሃይል ያልደረሰላቸው በመሆኑ፤ ማምረት የጀመሩ ፋብሪካዎች ከአቅም በታች ሲያመርቱ በዝግጅት ላይ ያሉት ደግሞ ወደ ምርት መግባት እንዳልቻሉ ተገለፀ።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የደብረብርሃን ከተማ ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንተናገሩት፤ በደብረ ብርሃን ከተማ እየተስፋፋ የመጣውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ፋብሪካ ገንብተዋል። ይሁንና የኤሌክትሪክ ሃይል ከዋናው ማሰራጫ ወደ ኢንዱስትሪ መንደሮቹ ማውጣት ባለመቻሉ 17 ማምረት የጀመሩ ፋብሪካዎች ከአቅም በታች ሲያመርቱ ለማምረት ዝግጁ የሆኑ 10 ፋብሪካዎች ደግሞ ወደ ሥራ መግባት አልቻሉም።
በአሁን ወቅት 29 ፋብሪካዎች የሃይል ችግር አጋጥሟቸዋል የሚሉት ከንቲባው፤ የሃይል እጥረት ያጋጠማቸው ፋብሪካዎችም በአንድ ፈረቃ ለስምንት ሰዓት ብቻ እየሰሩ ይገኛሉ። እነዚህ ፋብሪካዎች ታድያ የኤሌክትሪክ ሀይል ሙሉ በሙሉ ቢያገኙ በሦስት ፈረቃ በመስራት ከ5ሺ እስከ 6ሺ የሥራ ዕድል መፍጠር ይችሉ ነበር።
ከሥራ ዕድል ፈጠራው ባለፈ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ የሚገኝ መሆኑን በመግለፅ የክልሉ መንግሥት ሊያግዝና ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል። ክልሉ እስካሁን ባለው ሁኔታ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ እገዛ አለማድረጉንና መብራት ላይ ያለው ድጋፍም አናሳ መሆኑን ተናግረዋል።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ያየህ አዲስ፤ ጥያቄው ትክክልና ተገቢ መሆኑን ገልፀው፤ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን በዋናነት አዲስ ማሰራጫ እንዲሠራ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም ከፌዴራል መንግሥት በተገኘው ትልቅ ድጋፍ የተሳካና በከተማዋ ለሚገኙትኢንዱስትሪዎች በቂ የሆነ ሃይል ያለው ማሰራጫ የተገነባ መሆኑን አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ ከዋናው ማሰራጫ የኤሌክትሪክ ሃይልን ለኢንዱስትሪ መንደሮቹ ፈጥኖ ለማሰራጨት ያልተቻለበት ዋናው ምክንያት፤ የክልሉ መንግሥት በተለይም በደብረብርሃን አካባቢ ከፍተኛ በጀት መድቦ ለተፈናቃይ አርሶ አደሮች በተገቢው መንገድ የካሳ ክፍያ ከመክፈሉ ጋር ተያይዞ የክልሉ መንግሥት የበጀት እጥረት ያጋጠመው በመሆኑ ነው ብለዋል።
ስለሆነም ቀሪውን ሥራ ባለሀብቶቹ እራሳቸው እንዲተባበሩ ከከተማ አስተዳደሩና ከባለሀብቱ ጋር በመነጋገር መተማመን ላይ መደረሱን ጠቁመዋል። በዚህም ጥቂቶቹ የኤሌክትሪክ ሀይሉን ወደ ኢንዱስትሪ መንደሮቹ በመሳብ ወደ ሥራ እየገቡ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ መንግሥት ውል ገብቷል ግዴታ አለበት በሚል አንዳንዶቹ ወደ ስራው ፈጥነው ላለመግባት ምክንያት የሚያደርጉ ባለሀብቶች አሉ የሚሉት ኃላፊው፤ በትክክል ማልማት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ደግሞ ወደፊት መንግሥት ያካክስልናል በማለት በራሳቸው ወጪ እያስገቡ ይገኛሉ ብለዋል። ስለዚህ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ባለሀብቶቹ በተናጠልም ይሁን በጋራ እራሳቸው ቢያስገቡና ወደ ሥራ ቢገቡ መልካም እንደሚሆን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2012
ፍሬህይወት አወቀ