አዲስ ዘመን፡- የዳኝነት ሥርዓቱ በበጀት እጥረት እየፈተነው በመሆኑ የፍትህ አሰጣጡ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች ተናገሩ፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳሳ ቡልቻ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፤ መንግሥት ልክ እንደጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤት ለፍርድ ቤት ብዙ ጊዜ ትኩረት አለመስጠቱ እና የሚመድበውም በጀት አነስተኛ መሆኑ የፍትህ ሥርዓቱ ጥራት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡
የፍትህ አገልግሎት እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ታሳቢ አይደረግም የሚል እምነት እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ዳሳ፤ በእርግጥ ህዝብ የጤና፣ የውሃም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲሟሉለት የሚጠይቅ ቢሆንም ፍትህ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑ ታውቆ አስፈላጊው በጀት ሊያዝለት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
‹‹አንዳንድ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጠው በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ነው፡፡›› የሚሉት አቶ ዳሳ፤ በኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች የሚሰጠው በጀት አነስተኛ በመሆኑ የሥራ መሣሪያ ግብዓት አቅርቦት (ሎጀስቲክ) ላይ ከፍተኛ ችግር እያጋጠመ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ ከወረቀትና ከኮምፒውተር ጀምሮ በጣም ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን ሥራው ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩ እጥረቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አጋም በበኩላቸው፤ ጥራት ባለው መልኩ ለመፃፍ እንኳን ከኮምፒውተር ጀምሮ የሥራ መሳሪያ ግብዓት አለመሟላት ችግር እየፈጠረባቸው እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
ሪከርድ ለማድረግ (ለመቅዳት) የግብዓት እጥረት እንደሚያጋጥም በመጥቀስ፤ መስክ በመውጣት የሚሰሩ ሥራዎችን ለማከናወም የመኪና እጥረት እየፈተናቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይህም የግብዓት እጥረት ዳኝነቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሩን እና ተገልጋዮች እንዲንገላቱ በር መክፈቱን ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 18/2012
ምህረት ሞገስ