አዲስ አበባ፡- የፓስፖርት አሰጣጥ ቀን መርዘም ምክንያት ደላሎች በህገወጥ መንገድ እናስፈፅማለን በማለት ገንዘብ እንደሚወስዱ በመረጃ ደረጃ እንጂ ለኤጀንሲው የቀረበ ጥቆማም ሆነ አቤቱታ አለመኖሩን የኢምግሬሽን የዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው ሙስና ሰርተዋል የተባሉ ሰራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዱንም ጠቅሷል።
የኢምግሬሽን የዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ደሳለኝ ተሬሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ከፓስፖርት መዘግየት ጋር በተያያዘ ለሙስና የተጋለጡ አሰራሮች እንዳሉ ይሰማል። በተለይ በር ላይ ደላሎች በህገወጥ መንገድ እናስፈፅማለን በማለት ገንዘብ ያጭበረብራሉ ይባላል። ነገር ግን በማስረጃ የተደገፈ ለኤጀንሲው የቀረበ ጥቆማም ሆነ አቤቱታ የለም።
እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ፤ የፓስፖርት እጥረቱ ለመፍታት አንድ ሚሊዮን ፓስፖርት ታዞ በውጭ ህትመት ላይ ይገኛል። አጠቃላይ ሚያዝያ ወር ላይ ተጠቃሎ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። በክልል ከተሞች ሆሳህና፣ ነቀምት እና አሶሳ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት በመክፈት ለህብረተሰቡ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለማዳረስ እቅድ ተይዟል።
ኤጀንሲው በቂ ባይሆንም አገልግሎቱን ግልፅ ለማድረግ በተለያዩ መንገዶች በባነር፣ በማህበራዊ ድረገፅ፣ በእስክሪን ገለፃ እንደሚያደርግ ተናግረው፤ በነፃ የስልክ ጥሪም 8133 መረጃ መስጠት እንደሚቻል አመልክተዋል።
በደላላዎች አካባቢ የሚነሱትን ችግሮች ለማስ ተካከል እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ያመለ ከቱት አቶ ደሳለኝ፤ በቅርቡ ከሙስና ጋር በተያያዘ በውስጥ ሰራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱንም አስረድተዋል።
እንደ አቶ ደሳለኝ ገለፃ፤ የፓስፖርት አሰጣጥ በተመለከተ ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች የታደሰ መታወቂያ በመያዝ መውሰድ ይችላሉ።
ከ18 ዓመት በታች የሆኑት በልደት ሰርተፍኬት ብቻ ማውጣት ይችላሉ። መደበኛ ፓስፖርት በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ይሰጣል። በሌላ በኩል አስቸኳይ ፓስፖርት እንደየ ሁኔታው በአንድ ቀንም ወይም እስከ አምስት ቀን ሊሰጥ ይችላል። የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው፣ ቪዛ የተላከላቸው፣ ለህክምና፣ ለመንግስት ስራ ዎች፣ አስመጪና ላኪዎች በአስቸኳይ ፓስፖርት ይስተ ናገዳሉ።
በሕገወጥ መንገድ አገር ውስጥ የቆዩ የውጭ ዜጎች ተመዝግበው ድጋፍና ትብብር እንዲደረግላቸው ኤጀንሲው ባቀረበው ጥሪ መሰረት በሩብ አመቱ 125 የውጭ አገር ዜጎች /ዲያስፖራን ጨምሮ/ እንዲመዘገቡ መደረጉን ጠቅሰዋል። ከነዚህ ውስጥ 48 ውሳኔ የተሰጣቸው ሲሆኑ 77 ደግሞ ጉዳያቸው ተጣርቶ ውሳኔ እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 252 የውጭ አገር ዜጎች በተደረገው የቁጥጥር ስራ የተያዙ ሲሆን፤ በአማካይ እስከ 433 ሺ 940 ዶላር ውዝፍ እንዲከፍሉ በማድረግ ወደ ሀገራቸው ዲፖርት መደረጋቸውን አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ጥትቨ18/2012
መርድ ክፍሉ