አዲስ አበባ፡- በአዲሱ የትምህርት ስርዓትና በሚተገበረው ፍኖተካርታ መሰረት ልዩ ተሰጥኦ ላላቸው ተማሪዎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሚከፈት ተገለፀ፡፡
የቀድሞ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በአዲሱ የትምህርት ስርዓትና በሚተገበረው ፍኖተካርታ መሰረት አገሪቱ ለተሻለ የፈጠራ አቅም የምትበቃው በክፍል ውስጥ ተፈትነው 100 እና 90 በሚያመጡ ጎበዞች ብቻ አይደለም፡፡ ልዩ የተፈጥሮ ጸጋ ያላቸው ተማሪዎች እውቀታቸውን በተግባር የሚፈትኑበት እድል እንዲያገኙ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይከፈትላቸዋል፡፡
የልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ መኖር የተለየ ተሰጥኦ ባለቤት ተማሪዎች በፍላጎታቸው መሰረት እንዲማሩ ያደርጋል የሚሉት ዶክተር ጥላዬ፤ የአገሪቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አቅጣጫን ለማስተካከልም እድል እንደሚፈጠር ጠቅሰዋል፡፡
የትምህርት ፍኖተካርታውን ለመተግበር ከአስር እስከ አስራ አምስት ዓመታት የሚፈጅ በመሆኑ በአግባቡ ከተሰራበት ስራዎች ሁሉ በእውቀትና በባለሙያዎቸ እንዲመሩ እድል እንደሚፈጠር ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዶክተር ጥላዬ ገለፃ፤ ትምህርት ቤቱ መከፈቱ አገሪቱ የሚኖራትን ልማትና ግንባታ በማፋጠን ከዓለም ህዝብ ጋር ተወዳድሮ የማሸነፍን ሀይል ይሰጣል፡፡ በትምህርት ቤቱ የሚማሩት የልዩ ተሰጥኦ ባለቤቶችም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ የሚቀዱ፣ የሚያላምዱና የሚፈጥሩ እንዲሆኑ እድል ያገኛሉ፡፡
ይህ ትምህርት ቤት ከአሥር ዓመት በኋላ በመንገድ ሥራ፣ ኢንዱሰትሪዎችን በራስ አቅም የሚገነቡና የሚመረቱባቸው እንዲሆኑ እንዲሁም ሳተላይት የሚያመጥቅ ትውልድ ለመፍጠር ወሳኝ ሚና አለው፡፡
አዲስ ዘመን ጥትቨ18/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው