አዲስ አበባ፡- በ2012 በጀት አመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት በመደበኛና በመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለ734 ሺህ 226 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን የፌደራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዳይሬክተር አማካሪ አቶ አሰፋ ፈረደ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ 1.8 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ በመጀመሪያ ስድስት ወራት ለ734 ሺህ 226 ዜጎች በመደበኛና በመንግሥት ታላቅ ፕሮጀክቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 59 ሺህ 834 የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ተመራቂ ተማሪዎች ናቸው፡፡
ኤጀንሲው በንግድ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስ ትራክሽን፣ በከተማ ግብርና በአገልግሎት ዘርፎች ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፤ የስራ እድል የሚፈጠርላቸው ዜጎች በኢንተርፕራይዞችና በመንግስት ድጋፎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡
እንደ አቶ አሰፋ ገለጻ፤ የስራ እድል የተፈጠ ረላቸው ዜጎች ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት አጫጭር ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በስራ ከተሰማሩ በኋላም ዘመናዊ የሂሳብ አያያዝ፤ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የቁጠባ ባህል እንዲኖራቸው ድጋፍና ክትትል የሚደረግላቸው መሆኑንም ያብራራሉ፡፡
በተጨማሪም ለ11 ሺህ 232 ኢንተርፕራይዞች ለመስሪያ የሚያገለግሉ 1 ሺህ 642 ሼዶችን ለማስተላለፍ ተችሏል፡፡ የመስሪያ ቦታዎች በሁለት መልኩ የሚዘጋጁ ሲሆን ከአምስት ዓመት በፊት የስራ እድል የተፈጠራላቸው ዜጎች ከተገለገሉበት በኋላ ለሌላው የሚያስተላልፋበትና አዳዲስ ሼዶች ተሰርተው የሚተላለፉበት ሂደት መኖሩ አቶ አሰፋ ተናግረዋል ፡፡
ለኢንተርፕራይዞች የሚያመርቱዋቸውን ምር ቶች ለህብረተሰቡ ለማድረስ በአብዛኛው በመንግሥት በሚወጡ ጨረታዎችና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ለ58 ሺህ 5 ኢንተርፕራይዞች የብር 8 ነጥብ 5 ቢሊዮን የገበያ ትስስር ለመፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
የስራ እድል የተፈጠረላቸውን ዜጎች ከመደገፍ አንጻር ዘርፉን የሚመሩ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት የመስራት ውስንነት መኖሩን ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥትቨ18/2012
ወርቅነሽ ደምሰው