አዳማ፡-የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ከሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየመከሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ለ17 ቀናት የሚካሄደውና ከየክልሉ የተወከሉ ከሁለት ሺ በላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) ትናንት በይፋ ተጀምሯል፡፡
የፓርቲው ጽህፈት ቤት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መለስ አለሙ ስለ ስልጠናው ለጋዜጠኖች እንደገለጹት፤ ስልጠናው ከሕግ የበላይነትና ከሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና ሕብረተሰቡ ከለውጡ የሚጠብቀውን ውጤት እንዲያገኝ ለማድረግ የሚያግዝ ነው፡፡
እንደ አቶ መለስ ገለጻ፤ ስልጠናው ከሕግ የበላይነትና ከሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ምክክር የሚደረግበት ነው።ለሀገራዊ ለውጡ ሳንካ ሊሆኑ የሚችሉ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ፣ የመደመር እሳቤና ተግባር ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ እንዲያዝም ያደርጋል።
ሕብረተሰቡ ከለውጡ የሚጠብቀውን ውጤት እንዲያገኝ በሚያስችሉ ጉዳዮች አተኩሮ እንደሚመክርም አቶ መለስ አብራርተዋል።ከፍተኛ አመራሩ የነበሩ ጉድለቶችን በጥልቀት በመገምገም በቀጣይ የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመፍታት እንደሚረዳውም ጠቁመዋል።ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች አተኩሮ ይመክራልም ሲሉ ተናግረዋል።
የሕዝቦችን ችግሮች በጋራ የሚገነዘቡበት እና ችግሮቹን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል የጋራ አስተሳሰብ ለመያዝ በሚያስችል ሁኔታ ላይ እንደሚወያዩም ተናግረዋል።
አመራሮቹ በየደረጃው ከመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚመክሩበት ይሆናል ያሉት ኃላፊው፤ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችና ተግዳሮቶችን ማለፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ አቅም ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።
አመራሮቹ እርስ በእርስ የሚማማሩበትና የሚተዋወቁበት መድረክ እንደሚሆንም እምነታቸውን ገልጸዋል።የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ምንነትና ባህሪውን እንዲገነዘቡ እንደሚያደርግ በመጠቆምም፤ የተገኙ ስኬቶችን ባግባቡ ተገንዝበው ማስፋት የሚችሉበት እና ክህሎታቸውን እንደሚያዳብርም ጠቁመዋል።
መድረኩ የብልጽግናን ፓርቲ መሰረታዊ አቅጣጫዎች እና ዓላማ ላይ እንደሚወያይም ጠቁመዋል።ኢትዮጵያን ካለችበት ሁኔታ በማውጣት ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር እና የተጀመረውን ራእይ እውን ለማድረግ አመራሩ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ትኩረት ተደርጎ እንደሚመክርም ገልጸዋል።ውይይቱ የሚኖሩ ስጋቶችን ተጋፍጦ የትግል ምዕራፎችን በማለፍ ወደ በለጸገች አገር ለማሸጋገር እንደሚረዳም ጠቁመዋል።
እንደእርሳቸው ገለጻ፤ አመራሩ በቆይታው በዓመቱ በሚኖሩ ሕዝባዊና መንግሥታዊ ስራዎች ኃላፊነቱን በሚወጣበት ሂደት ላይ አተኩሮ ይመክራል።ቀጣዩን ምርጫ አሸንፎ የሚወጣ ከሆነም፤ የፓርቲው ስራዎች በሚከናወንበት ስልትና ወደፊት ለሕብረተሰቡ ይፋ በሚደረጉ መሰረታዊ አቅጣጫዎች አመራሩ መግባባት ላይ ይደርሳል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሩ ስልጠና የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መለስ፤ የሕዝቡን የለውጥ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባት እንደሚጠቅም አክለዋል።ለቀጣይ ተልዕኮ ለማዘጋጀት እንደሚረዳም ጠቅሰዋል።ዓላማውን ለማሳካት አመራሮቹ በቆይታቸው የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንደሚመክሩም አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 17/2012
ዘላለም ግዛው