አዲስ አበባ፡- በዘንድሮው ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን በተለያየ መልኩ ለማካተትና ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ በተለይ በብሬልና በምልክት ቋንቋ መጠቀም እንዲቻል የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽንን በመያዝ ሥራዎች በማከናወን ላይ መሆኑን የምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የምርጫ ቦርድ አባል የሆኑት ዶክተር ጌታሁን ካሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም በእኩል ደረጃ መረጃ የሚያገኝበት ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። የምርጫ አሰራሮችም ለሁሉም በፍትሀዊነት ማዳረስ ተገቢ ነው። ስለሆነም በዘንድሮው ምርጫ አካል ጉዳተኞችን ተሳታፊ ለማድረግ የብሬልና የምልክት ቋንቋ በምርጫ ሥርዓቱ ውስጥ ተካተው እንዲሰራባቸው ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በማንኛውም ቦታ የአካል ጉዳተኞች ተዘዋውረው እንዲመርጡና ተመራጭም ከሆኑም እንዳይቸገሩ ለማድረግ ቦታዎችን ምቹ ለማድረግ መታሰቡን የጠቀሱት ዶክተር ጌታሁን፤ ከብሬል ዝግጅቱ ባለፈ በመገናኛ ብዙሃን በኩል መረጃዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ተመራጮች ፕሮግራማቸውንና ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ በምልክት ቋንቋ ጭምር ሀሳባቸውን እንዲገልጹ ለማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ስራው የተሳካ እንዲሆን ከፓርቲዎች ምዝገባ እንደጀመሩ የሚናገሩት ዶክተር ጌታሁን፤ ፓርቲዎች 20 በመቶ የአካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ ሥራ እንዲሰሩ ተደርጓል። አይነስውራን አርማዎችንም ሆነ ሌሎች በእነርሱ ደረጃ መታወቅ ያለባቸውን ነገሮች ተረድተው የሚመርጡበት ሁኔታ ለማመቻቸትም ብሬሎች ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማህበር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ድባቤ ባጫ በበኩላቸው የቴክኖሎጂ ዝግጅት በተወሰነ ደረጃ ከማህበራቸው ጋር መስራት መጀመሩን ገልጸው፤ ፕሮግራሞች ላይም የሚመርጡትን ሰው እንዲያውቁት እና በምርጫ ጣቢያዎች ላይ የራሳቸውን ሰው እንዲያመጡ ለማድረግ የምልክት ቋንቋን ማካተቱ ለአካል ጉዳተኞች ያለው ዋጋ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም ብለዋል። አካል ጉዳተኞች መብታቸው ተጠብቆ በፍላጎታቸው መምረጥ እንዲችሉ ስለሚያግዝ ብሬልና የምልክት ቋንቋ በምርጫ 2012 ጥቅም ላይ ለማዋል መታሰቡ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
የብሬል ዝግጅቱ መኖር አይነስውራን ከዚህ በፊት እንደሚያደርጉት የሚመርጡትን ሌላ ሰውን አሳውቀው ስለሚሆን የመረጡት ሰው በትክክል መመረጡንም አያረጋግጡም። አሁን ግን ይህ ችግር ሙሉ ለሙሉ እንዲጠፋ ያደርጋል የሚሉት ወይዘሮ ድባቤ፤ ማንም ሰው የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት እንዳለው እንዲረዱና የመረጡት ሰው ትክክል እንደሆነ እንዲያረጋግጡም ያደርጋቸዋል ብለዋል።
እንደ ወይዘሮ ድባቤ ገለጻ፤ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በእስከዛሬው ምርጫ ተሳትፏቸው የሚታይ አይደለም። የትኛውን ፓርቲ እንደሚመርጡም አያውቁም ነበር። እነርሱም ቢሆን ለመምረጥ አድሜያቸው ቢፈቅድም መሳተፍ አይችሉም። ይህ ደግሞ ለዘመናት በተጽዕኖ ውስጥ እንዲያልፉ አድርጓቸዋል። አሁን ግን በምልክት ቋንቋ የተለያዩ መረጃዎች እንዲያገኙ ለማስቻል መታሰቡ ይህንን ችግራቸው እንደሚቀርፍላቸው ገልጸዋል።
መስማት የተሳናቸው ሰዎች ችግር ሰፋ እንጂ ሌላውም የአካል ጉዳት ላይም በምርጫ ዙሪያ ብዙ ተጽዕኖዎች አሉበት የሚሉት ወይዘሮ ድባቤ፤ አሁን ላይ እነዚህ ነገሮች መታሰባቸው በጥቂቱም ቢሆን መፍትሄ ይሰጣል። መረጃዎች ለሁሉም በእኩል ደረጃ ደርሰው በፍላጎታቸው የሚመርጡበት እድል ይፈጥርላቸዋል። ቀደም ሲል የነበረውን አካታች ያለመሆን ሁኔታን እንዲለወጥ እድል እንደሚሰጣቸው አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 17/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው