• የችግኝ ተከላና የደን ልማቱ አሰራር እንዲቀየር ተጠይቋል
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በስድስት ዓመታት በችግኝ አለመጽደቅ 65 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መክሰሯ ተገለጸ። የዘርፉ ባለሙያዎች የችግኝ ተከላና የደን ልማት አካሄድ አገሪቱን ለኪሳራ እየዳረጋት በመሆኑ እንዲቀየር ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ውብዓለም ታደሰ፤ አገሪቱ ከ2006 እስከ 2011 ዓ.ም 24 ነጥብ 1 ቢሊዮን ችግኝ መትከሏን ይናገራሉ። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በተደረገው የጽድቀት የዳሰሳ ጥናት ከ50 እስከ 59 በመቶ መጽደቁ ያረጋግጣሉ። ይህም በአማካይ 54 ነጥብ 5 በመቶ ነው። በዚህ መሰረትም ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተተከለው ችግኝ ውስጥ 10 ነጥብ 96 ቢሊዮኑ ችግኝ ደርቋል ማለት ነው።
የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የከተማ ደን ልማትና አያያዝ ባለሙያ አቶ ዘላለም አዲስ፤ አንድ ችግኝ ከማፍላት እስከ ተከላ ስድስት ብር እንደሚያስወጣ ያመለክታሉ። በዚህ አሀዝ መሰረት ባለፉት ስድስት ዓመታት ያልጸደቀው ችግኝ ሲሰላ አገሪቱ 65 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መክሰሯን ያሳያል።
ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ባለፉት ሶሰት ዓመታት በአማካይ 70 በመቶ ጽድቀት እንዳለ ቢያሳይም ይህ ትክክል አለመሆኑን ዶክተር ውብዓለም አንስተዋል። “የደን ልማት ዘርፍ የተረሳና ትኩረት የተነፈገው ነው።
ዘርፉ ህዝብ ያለማዋል በሚል መንግስትና ባለሃብቱ የማይሳተፍበት ነው። አደረጃጀቱም በግብርና ሚኒስቴርና በኮሚሽኑ ለሁለት ተከፍሎ እንዳይሰራ ሆኖ የተዋቀረ ነው። ችግኝ ቢተከልም እንክብካቤ የሚደረግበት አሰራር የለም። በዘመቻ የሚተከሉ ችግኞች በአብዛኛው አይጸድቁም። ችግኞች የሚተከሉት በዓላማ አይደለም” ብለዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ከሚተከለው ችግኝ ሰማኒያ በመቶው ከመደብ ላይ ተነቅሎ የሚተከል ነው። ያለ አፈር ከመደብ ላይ ተነቅሎ የሚተከል ችግኝ በአብዛኛው አይጸድቅም። ከሚተከለው 90 በመቶ የሚሆነው ባህር ዛፍ ነው። አገር በቀል ዛፎችም እየጠፉ ነው።
በባለሙያዎች በእውቀት የተደገፈ የደን ልማትም እየተካሄደ አይደለም። አገሪቱ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ ብትተክልም በሚፈለገው ደረጃ አልጸደቀም። አሁን እየተሄደበት ያለው መንገድ ውጤታማ ስላላደረገን መንግስት አካሄዱን መቀየር አለበት።
እንደ ዶክተር ውባለም ገለጻ፤ የአገሪቱ የደን ልማት ውጤታማ ባለመሆናቸው ትላልቅ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች በደለል እየተሞሉ 50 ዓመታት ማገልገል ሲገባቸው ሃያ ዓመታት ሳያገለግሉ በደለል ከጥቅም ውጭ እየሆኑ ነው። አገሪቱ በየዓመቱ የእንጨት ውጤቶችን ለመግዛት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታወጣለች። በተደጋጋሚ በድርቅም እየተጠቃች ትገኛለች።
በኢንስቲትዩቱ የዋና ዳይሬክተሩ አማካሪ ዶክተር ተሾመ ለማ፤ በበኩላቸው የሚተከሉ ችግኞች አረም፣ ኩትኳቶ፣ የበሽታ መከላከልና ውሃ የማጠጣት እንክብካቤ አይደረግም። በየዓመቱም በዘመቻ ቀደም ባለው ዓመት ተተክሎ በደረቀው ቦታ መልሶ ይተከላል። ችግኝ ሲተከል ለማገዶ፣ ለምርት፣ ለመኖ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለውበትና ሌሎች ስራዎች ተለይቶ ስለማይተከል የደን ልማቱ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ስላልሆነ አካሄዱ መስተካከል እንዳለበት እሳቸውም ይናገራሉ።
በአማራ ክልል በግላቸው ለ30 ዓመታት በ18 ሄክታር መሬት የደን ልማት ያካሄዱት አርሶ አደር ሙሉዓለም ብርሃኑ፤ መንግስት እየተከተለ ያለው የደን ልማት ከፈረሱ ጋሪው የቀደመ ነው። ፖሊሲና ስልት ሳይነደፍ በዘመቻ ችግኝ ያስተክላል። ባለፉት ዓመታት በየዓመቱ በዘመቻ ቢያስተክልም ውጤት ጠብ አላደረገም።
አሁን ባለው አካሄድ ደን እናለማለን ማለት ወሬ ነው። እንኳን ተክሎ ማጽደቅ አይደለም ያለውን ደንም አልተንከባከበም። መንግስት ከወሬ፣ ከሪፖርትና ከማስመሰል ወጥቶ መሬት ጠብ የሚል ስራ መስራት አለበት። በህልውናችን ላይ የተጋረጠው የድርቅ አደጋ እውነተኛ መፍትሄ ያስፈልጋዋል ብለዋል።
የስነ ምድርና የታዳሽ ሀይል ባለሙያ ዶክተር ብርሃኑ ግዛውም፤ ኢትዮጵያ በስነ ምድር እንክብካቤ እጦት በከፋ ችግር ውስጥ ትገኛለች። አሁን የሚታየው የደን ልማት እንቅስቃሴ እሳት የማጥፋት ስራ ነው። ለችግሩ በቂ መልስ አይሆንም። ሁሉም ነገር ከደን ጋር የተያያዘ በመሆኑ ውጤታማ ለመሆንና ችግሩን ለመመከት በልዩ ሁኔታ መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
የኮሚሽኑ የከተማ ደን ልማትና አያያዝ ባለሙያ አቶ ዘላለም፤ ቀደም ሲል ተክሎ ያለመንከባከብ ችግር እንደነበር ጠቁመው ይህን ችግር ቀርፎ የችግኝ ጽደቅትን ለማሳደግ አራት ተቋማት በማቀናጀት እንክብካቤ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል። ከተከላ በኋላ ያለውን መቀዛቀዝ በማነቃቃት እንክብካቤ ይደረጋልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ያላት የደን ሽፋን 15 ነጥብ 5 በመቶ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 10 በመቶ በቆላማ አካባቢ በሳርና በቆላ ዛፎች የተሸፈነ ነው። ሰው ሰራሽ ደን ከአንድ በመቶ ብዙም ያላለፈ ነው። አገሪቱ በየዓመቱ ከ80 እስከ 90 ሺ ለሰፋፊ የእርሻ መሬትና ለሌሎች አገልግሎቶች ደንን ትመነጥራለች።
አዲስ ዘመን ጥር 17/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ