-ጠቅላይ ምክርቤቱ ህጋዊ እውቅና በማግኘቱ መደሰቱንም ገልጿል
አዲስ አበባ፡- ህዝበ ሙስሊሙ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱበትን ችግሮች በትዕግስት አልፎ ለአገር ሰላም ወሳኝ አስተዋጽኦውን እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ። ለምክርቤቱ ህጋዊ እውቅና በመሰጠቱ መደሰቱንም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር እንድሪስ በሞጣ አካባቢ በደረሰው ችግር ዙሪያ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚል ጉዳይ ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የሙስሊሙ ደስታ የክርስቲያኑም ደስታ ነው። የሙስሊሙም ሀዘን የክርስቲያኑ ሀዘን ነውና ሰሞኑን በተሰጠው እውቅና እኛ በመደሰታችን ደስታው የጋራ ይሁን ብለዋል።
በተለያየ አጋጣሚ ችግሮች ይከሰታሉ። ሆኖም መቻቻልንና ወደ አንድነት መምጣትን የሚያክል ነገር የለም። ስለሆነም ህዝበ ሙስሊሙ የለመደውን የሰላም ሥራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ፤ ለዘመናት ብዙ ጥቅም ሊገኝበት ይገባ የነበረው እውቅና ሁኔታ እስከዛሬ ሳይሳካ ቀርቷል። ሆኖም አሁን ምላሽ በማግኘቱ ከመንግሥት ጀምሮ ያሉ አካላት ምስጋና ይገባቸዋል። ከዚያም ባለፈ ሥራው የሙስሊም
ማህበረሰቡ ብቻ ባለመሆኑ ክርስቲያን ወንድሞችም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። በዚህም ደስታው የጋራ ነውና እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ሼህ ኢዲን ደሊል በበኩላቸው፤ ህዝበ ሙስሊሙ በተለያዩ አካባቢዎች ብዙ ችግሮች እየደረሰበት ነው። ይሁንና በትዕግስት ማለፍ ካልተቻለ ብዙ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉና ህዝበ ሙስሊሙ የሚደርሱበትን ትንኮሳዎች በትዕግስት ሊያልፈው ይገባል። ከዚህ ቀደም ሲያደርግ የነበረውን የአገር ሰላም ጥበቃ አሁንም በችግር ውስጥ ሆኖ ወሳኝ አስተዋዕጾውን ማድረግ አለበት። ለዚህም ከጠቅላይ ምክርቤቱ የሚሰጡ አቅጣጫዎችን መከተል ይኖርበታል ብለዋል።
በሞጣ አካባቢ የደረሰውን ችግር ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ያሳሰቡት ሼህ ኢዲን፤ ተጎጂዎች የመስገጃና ሌሎች የሀይማኖት ጉዳዮች ማስፈጸሚያ ቦታና የሚተዳደሩበት ገቢ የላቸውም። በመሆኑም ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን ወስዶ ድጋፍ ለማሰባሰብ አስቧል።
ድጋፉ የሚጀምረውም በሚቀጥለው ጁምዓ ማለትም ጥር 22/2012 ዓ.ም ነው። ለዚህ ያግዝ ዘንድ የቻለ በክልል፣ ዞንና ወረዳ እንዲሁም ዋና መስሪያ ቤት መጥቶ ማድረስ ይችላል። ያልቻለ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000315148457 በመጠቀም ገቢ ማድረግ እንደሚችል ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 17/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው