– ገቢዎች ሚኒስቴር የዕቅዱን 101 በመቶ አሳክቷል
አዲስ አበባ፡- በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ሀሰተኛ ደረሰኝ በሚጠቀሙና በግብይት ወቅት ደረሰኝ በማይቆርጡ 130 ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ። ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው 191 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረገ ሲሆን በታክስ አስተዳደር አዋጅ መሰረትም ድርጅቶቹ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እንዲቀጡ መደረጉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገቢዎች ሚንስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ በግብይት ወቅት ደረሰኝ የማይቆርጡ ድርጅቶችን የኢንተለጀንስ ጥናት በመጠቀም ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፤ በዚህም ሀሰተኛ ደረሰኝ ሲጠቀሙ በተገኙና በግብይት ወቅት ደረሰኝ በማይቆርጡ 130 ድርጅቶች ተደርሶባቸው በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው 191 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረገ መሆኑን ሚኒስትሯ የተናገሩ ሲሆን፤ በታክስ አስተዳደር አዋጅ መሰረትም ድርጅቶቹ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር እንዲቀጡ መደረጉን አስታውቀዋል።
ሚኒስትሯ አክለው እንደገለጹትም፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2012 በጀት ዓመት ስድስት ወራት 125 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 127 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 101 በመቶ አሳክቷል። የዕቅድ አፈፃፀሙ
ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ28 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሲሆን የ29 በመቶ ዕድገትም አሳይቷል። በስድስት ወራት ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 58 በመቶ ከሀገር ውስጥ ገቢ ሲሆን ቀሪው 42 በመቶ የሚሆነው ከጉምሩክ ገቢ የተሰበሰበ ነው። ለዕቅዱ መሳካት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ሠራተኞችና ታማኝ ግብር ከፋዮች እንደሆነ ተገልጿል።
ግብር ከፋዮች ሳይገደዱ በፍላጎታቸው እየከፈሉ መሆናቸውን ወ/ሮ አዳነች አስታ ውሰው፤ ለህግ ተገዢ ያልሆኑትን ግብር ከፋዮች ወደ ትክክለኛ መስመር ለማምጣት ጠንካራ የህግ ማስከበር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2012
ዋለልኝ አየለ