አዲስ አበባ፡- ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ300 በላይ በውሃ ነክ ሥራዎች የተሰማሩ የግል ተቋራጮች ንግድ ፈቃዳቸውን መመለሳቸውን የኢትዮጵያ ውሃ ነክ ሥራዎች ግንባታ ተቋራጮች ማህበር አስታወቀ።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ታገሰ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውሃው ዘርፍ ከተሰማሩ ሥራ ተቋራጮች፣አማካሪዎች ፣እቃ አቅራቢዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገው ምክክር ትናንት በካፒል ሆቴል በተጀመረበት ወቅት እንዳሉት፤ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በተለይ ጥቅምት 2010 የተደረገውን የውጭ ምንዛሬ ለውጥ ተከትሎ የግንባታ እቃ ከውጭ የሚያስፈልጋቸው ተቋራጮች በሙሉ ህልውናቸው ተፈትኖ ቆይቷል።
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ባለፈው ዓመት በተጨባጭ መረጃ በአንድ ዓመት ብቻ በሦስት ክልሎች በተሰበሰበ ዳታ መሰረት በአማራ ክልል 28 ተቋራጮች የያዙትን የውሃ ፕሮጀክት አቋርጠዋል።በኦሮሚያ ክልል 45 በንጹህ መጠጥ ውሃና 17 በመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ ይሰሩ የነበሩ ተቋራጮች በድምሩ የ62 እንዲሁም በደቡብ ክልል የ26 ተቋራጮች ውል ተቋርጧል።
‹‹ከውጭ ምንዛሬ ለውጡ ጋር በተያያዘ በተለይ ተቋራጮችና አቅራቢዎች ከፍተኛ ጉዳት ዶርሶብናል››ያሉት ፕሬዚዳንቱ በዚህም ከ300 በላይ ድርጅቶች ንግድ ፈቃዳቸውን መመለሳቸውን አስታውቀዋል። ‹‹በችግሩ ሳቢያ በርካታ ሠራተኞቻችንን ለመበተን ተገደናል ፣በዚያው ወድቀው የቀሩም አሉ፤እንደምንም ተነስተው የቆሙም አሉ››ሲሉ ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል።
የውጭ ምንዛሬ ለውጡ ከውጭ ሀገር ብቻ የሚመጡ ቧንቧዎች፣ ፓምፖች፣ ፉቲንጎች፣ ወዘተ ለማስገባት ችግር ሆኖ መቆየቱንም ጠቅሰው፣ በዚህ ሳቢያም ፕሮጀክቶቻቸውን በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለማጠናቀቅ እንዳልቻሉም ተናግረዋል።
‹‹አሰሪዎቻችን ችግሮቻችንን ይሰማሉ፤ችግሩን እናውቀዋለን ይላሉ፤አንዳንዴ ደግሞ መስማትም አይፈልጉም ››ሲሉ ገልጸው፣ሁሉም ወገን የኮንትራት አስተዳደር ዶክመንት የማንበብና የመተግበር ድክመት እንዳለበትም አመልክተዋል።
አማካሪዎችና አሰሪዎች ግን ማስጠንቀቂያ የመጻፍ ፣ የመቅጣት ፣ለመልካም አፈጻጸም ያስያዝነውን የባንክም ሆነ የኢንሹራንስ ገንዘብ ለመጠየቅ ውል ለማቋረጥም ድክመት አላሳዩም ሲሉ ያብራራሉ።ጥቂት የማካካሻ ገንዘብ ከፍሎ እና ጊዜን አራዝሞ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በመስኖ እና በንጹኀ መጠጥ ውሃ ግንባታ ላይ የሚሰሩት አብዛኞቹ ሀገር በቀል ተቋራጮች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
እነዚህ ተቋራጮች በአንድ በኩል ዋጋን በትክክል ከመገመት እና ከመሳሰሉት አኳያ በዲዛይን ፣በኮንትራት አስተዳደር ችግር እንደሚስተዋልባቸው ጠቅሰው፣በሌላ በኩል ተገቢ መሳሪያ አለመያዝ፣ አቅም ያለማደራጀት እና በቂ ፋይናንስ ይዞ ያለመነሳት ችግር እንደሚታይባቸው አብራርተዋል።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚያስፈልግና የተቋራጮቹ አቅም እንዲገነባ በርካታ ድጋፎችን ፣የግንባታ መሳሪያዎችን በበቂ መልኩ እንዲያገኙ እንዲሁም በቂ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ተቋራጮቹ በራሳቸውም የሚሰሩትን ሥራ በየወቅቱ መከታተል እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ ተናግረው፣ ስራቸውም እየተገመገመ ውጤት ላይ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ እና ፋይናንስ በበቂ ሁኔታ ሰርተው እንዲያስረክቡ ብርቱ ክትትል እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2012
ኃይሉ ሣህለድንግል