አዲስ አበባ፡- ጠንካራ የሆነ የዕፅዋት ቁጥጥርና ጥበቃ አለመኖር ሰብሎችና የፍራፍሬ ተክሎች በመጤ አረምና ባክቴሪያ እየተጠቁና ምርታማነት እንዲቀንስ እያደረገ መሆኑን ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ ችግሩ የቁጥጥር ማነስ ሳይሆን የአጠቃቀም ስርዓቱ ልቅ በመሆኑ የተከሰተ መሆኖኑን አመልክቷል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና መምህር ዶከተር አዳነ ተስፋዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመጤ አረምና በባክቴሪያ ምክንያት በሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው። ባክቴሪያውን መቆጣጠር ባለመቻሉ ምርትና ምርታማነትም እየቀነሰ ይገኛል።
በሁሉም የፍራፍሬ ተክል ላይ በሽታ መከሰቱን ዶክተር አዳነ ጠቅሰው፤ በተለይም የማንጎ ተክል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹ዋይት ስኬል›› በተባለ ባክቴሪያ በመጎዳቱ ከዘርፉ ይገኝ የነበረው ከፍተኛ ጥቅም እያሳጣ መሆኑን አስገንዝበዋል። ባክቴሪያው ከፊል የህይወት ዑደትን የሚከተልና ዕፅዋቱን በማቁሰል ፍሬው ከማፍራቱ በፊት እንዲረግፍ የሚያደርገው መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ዶክተሩ ማብራሪያ፤ ተባዩ አነስተኛ በመሆኑ በቀላሉ በንፋስ ከቦታ ቦታ በመዘዋወሩ የከፋ ችግር እያደረሰ ነው። ወደ ሀገርም ሊገባ የቻለው አነስተኛ የሆነ የቁጥጥር ስርዓት በመኖሩ ነው። ከውጭ የሚመጡ እፅዋቶችን ፈትሾና መርምሮ ማስገባት ያለመቻሉ ብዙ አይነት የነፍሳትና የአረም በሽታዎች በቀለሉ እንዲስፋፉ አድርጓል። በሁሉም የሀገሪቱ የመውጫና የመግቢያ ጠረፎች ላይ ያለው ቁጥጥር አናሳ መሆን ችግሩን አባብሶታል። የተቀናጀ የተባይና የአረም መከላከል ሥራ ባለመሰራቱም በሽታው ከክልል ክልል በፍጥነት ተዛምቷል።
በግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዮስ ሰላቶ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ ዋና ዋና መግቢዎችና በኤርፖርተሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ የቁጥጥር ስራዎች ይሰራሉ። የማንጎ ዋይት ስኬል በሽታ በዋናነት የተስፋፋው በቁጥጥር ማነስ ሳይሆን የአጠቃቀም ስርዓት ልቅ መሆኑ ነው።
ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶች በባለሙያ የሚፈተሹ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ሊገቡ የሚችሉ በርካታ አረሞችንና የባክቴሪያ በሽታዎችን መከላከል መቻሉን አስገንዝበዋል። «ከሌሎች ሀገሮች አንፃር የኛ ሀገር የቁጥጥር ሥራ ጥብቅና ዝግ ነው። እርግጥ ነው፤ ወደ ሀገር የሚገቡ ባለሀብቶችን ታማኝ ካልሆኑ በስተቀር በቁጥጥር ብቻ ማዳን ይቻላል ብለን አናስብም» ብለዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ አንዳንድ የዕፅዋት በሽታዎች በውጭ ባለሀብቶች ገብተዋል የሚባል ነገር ቢኖርም በጥናት የተረጋገጠ ነገር የለም። ከዛ ይልቅ በወፎችና በትራንስፖርት አማካኝነት እንደሚገቡ አመላካች ነገሮች አሉ። በሽታዎቹ ከተከሰቱ በኋላ ከቦታ ቦታ እንዳይሥፋፉ በሀገር ውስጥ ያለውን ቁጥጥር ለማጠናከር ክልሎች ደንቦችንና መመሪያዎችን ለማውጣት በሂደት ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2012
ሞገስ ፀጋዬ