ቦንጋ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ የቡና ምርምርን ለማጎልበት ታስቦ በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ በ35 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ብሄራዊ የቡና ሙዝየም ላለፉት አምስት ዓመታት ያለ ሥራ መቀመጡ እንዳሳሰበው የከፋ ዞን አስታወቀ።
የካፋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይ ተሰማ በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ደርጅት እንደገለፁት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ቡና እና ቡና ነክ የሆኑ የምርምር ሥራዎች እንዲካሄዱ ታስቦ በ2000 ዓ.ም ብሄራዊ የቡና ሙዝየም በቦንጋ ከተማ እንዲገነባ መወሰኑን አስታውሰው፤ በወቅቱ ከተማሪዎች፣ መምህራንና ህዝቡ 35 ሚሊዮን ብር ተሰብስቦ ግንባታው መከናወኑን አስገንዝበዋል።
የሙዝየሙ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላም በ2007 ዓ.ም በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት የምርቃ መርሐ ግብር መከናወኑንና በቡና ላይ የምርምር ሥራ አበክሮ እንዲሰራ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ምክትል አስተዳዳሪው አስታውሰዋል ይሁንና ከቡና መገኛ ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ የሆኑ ክርክሮች በመነሳታቸው ሙዝየሙ ሥራ ሳይጀምር ከአምስት ዓመታት በላይ መቆጠሩን ተናግረዋል።
እንደ አቶ በላይ ከሆነ፤ ከቡና መገኛነት ጋር በተያያዘ የሚነሳው አለመግባባት ለሙዚየሙ ሥራ አለመጀመር ዋነኛ ችግር ቢሆንም ችግሩን ለመቅረፍ እውነታውን የሚያረጋግጡ ጥናቶችንና ምርምሮችን በማካሄድ እልባት መስጠት የሚገባ ቢሆንም በፌዴራልም ሆነ በክልሉ መንግሥት ጉዳዩ ችላ የተባለ መሆኑን ጠቁመዋል።
ብሄራዊ የቡና ሙዝየሙ ዋነኛ ዓላማ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማካሄድ ስለሆነ ግንባታው በመጠናቀቁ ሥራው መካሄድ ነበረበት ያሉት አስተዳዳሪው በአሁኑ ወቅት ጎብኚዎችም ሙዝየሙን እየገበኙ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ ጉብኝቱ እየተከናወነ አይደለም፤ አስፈላጊ ግብዓቶችም የሉም ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።
አቶ በየነ እንደሚናገሩትም ሙዚየሙን ከማስ ተዳደር አኳያም ግልፅ ባለመደረጉ አስቸጋሪ ሆኗል። ቦንጋ ዩኒቨርሲቲም በዚህ ሙዝየም ውስጥ የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን ፍላጎት እንዳለው ቢገልፅም፤ ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩም ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል።
እንደ ምክትል ዋና አስተዳዳሪው ገለፃ፤ ችግሩን ለማቃለል ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ለክልሉ እና ፌዴራል መንግሥትም በተደጋጋሚ የማሳወቅ ሥራ ቢሰራም የተገኘ ተጨባጭ ምላሽ የለም። እነዚህ አካላት ጉዳዩን ተከታትለው መፍትሄ እንዲሰጡ ዞኑ መጠየቁንና አሁንም በድጋሚ እንደሚጠይቅ ገልፀዋል። ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑም የፌዴራል መንግሥት ትከረት በመስጠት እልባት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
ከዞኑ በተገኘው መረጃ መሠረት ፤ የካፋ ዞን ቀደም ሲል በተካሄደው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ 1ነጥብ5 ሚሊዮን ህዝብ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በገጠርና በከተማ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች እንደሚኖሩበት ይገመታል። በዞኑ 12 ወረዳዎች እና ሁለት ከተማ መስተዳድሮች የሚገኙ ሲሆን በሁሉም አካባቢዎች ቡና ይመረታል።
በዞኑ ከፍተኛ የሆነ የቡና ፣ ቅመማ ቅመምና የእንስሳት ሃብት መኖሩም ይታወቃል። ይሁንና በየወረዳው ያሉ ኢንቨስተሮች የቡና ኢንዱስትሪን ለማዘመን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በዞኑ ካለው የቡና ሃብት ጋር የተመጣጠነ አይደለም።
የመሰረተ ልማት አለመሟላት ደግሞ ለኢንቨስተሮች ቅሬታ የፈጠረባቸው ሲሆን ይህም ህብረተሰቡም ሆነ ሀገሪቱ ከዞኑ ከሚገኘው የቡና ምርት በተገቢው መልኩ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት መፍጠሩን አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር