አዲስ አበባ፡- በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የመንግሥት አወቃቀርን መነሻ በማድረግ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ችኮላ ሳይሆን የሰከነ ውይይት እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት ከክልሉ ከተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሁሉም ጉዳይ በአንድ ጀንበር መልስ መስጠት አዳጋች ነው። በተለይ በደቡብ ክልል የመንግሥት መዋቅር ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር ድረስ ከህብረተሰቡ ጋር ሰፊና የሰከነ ውይይት ማድረግ ይገባል።
ከደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡት የማህበረሰብ ከፍሎች የመንግሥት አወቃቀርን የሚመለከቱ ( ልዩ ወረዳ፣ ዞንና ክልል) የመሆን ጥያቄ፣ መሰረተ ልማትን የሚመለከቱ (መንገድ፣ መብራት፣ ጤና፣ ውሃ፣ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ትምህርት) የማግኘት ጥያቄዎች፣ የሰላም ጉዳይ (የጾታ ትንኮሳዎች፣ የቤተ እምነት ቃጠሎና ግጭቶች)፣ ወዘተ የተመለከቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀረቡ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽም፤ የደቡብ አካባቢ ህዝቦች ከ20 ዓመታት በላይ አንድ ክልል በመሆን በአንድነት መኖራቸውንና ክፉና ደጉን በጋራ ያሳለፉ የኢትዮጵያ ምሳሌ ተደርገው ተጠርተዋል። ቢሆንም አንድ ጊዜ ተወስኗል ከእንግዲህ በኋላ ክልል የሚባል ጥያቄ የለም ዝም ብላችሁ ኑሩ አይባልም። በየሰፈሩ ክልል ካልሆንኩ ለሚለውም ሁሉንም ክልል ማድረግ አይቻልም።
ምክንያቱም አቅም የለም። ችግሩንም መፍትሄውንም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማየት ይገባል። በዚህም ዘለግ ላለ ጊዜ የሚያገለግል አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ ነው። መንግሥት በክልሉ የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን እየፈታ መሆኑንና በሂደትም የሚታዩ ጉዳዮች መኖራቸውን፤ ለዚህም በየጊዜው ውይይት ማድረግ እንጂ ጥድፊያ እንደማያስፈልግ አመልክተዋል።
ክልል መሆን ይፈቀድልን የሚል ጥያቄ ቢነሳም ህገ መንግሥቱ ‹‹ብሄር የራሱ ክልል መመስረት ይችላል›› እንደማይልና ይልቁንም ብሄሮችና ብሄረሰቦች እንደ ጂኦግራፊ አቀማመጣቸውና እንደ ባህል ቅርበታቸው የየራሳቸውን ክልል መፍጠር ይችላሉ ስለሚል ጥያቄዎች ሲስተናገዱም ለብቻ ክልልና ወረዳ መሆን ሳይሆን ሌሎችንም በመጨመር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉን ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅ ችግሩን እንዴት እንፍታው በሚለው ሀሳብ ችኮላ ሳይሆን የሰከነ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ደቡብ በምን መልኩ ቢደራጅ ይሻላል የሚለውን ለመወሰንም ህዝቡን የሚጠቅም ውይይት በማድረግ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በየዞኑ፣ በየወረዳውና በየቀበሌው ማህበረሰቡን ሊያወያዩ የሚችሉ ቁጥራቸው 80 የሆኑ ከክልሉ የተወጣጡ ግለሰቦች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብልጽግና የሚያስበው ልማት ለኢትዮጵያ በቂ እንዳልሆነና ሌሎች ጋር ሠላምና ልማት ከሌላ እንኳን ክልል አገርም ለብቻ መልማት እንደማትችል በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያም እንደ አገር ከሌላ ጋር ሳትደመር መኖር እንደማትችልና ህዝቡ ይህንን በመረዳት የመልማት ጥያቄን የግል ብቻ ሳይሆን የጋራ ማድረግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
እየተጋገዙ መሄድ እንጂ ሰላም በምኞት አይመጣም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጥያቄን መሰረት አድርጎ የህዝብ ሀብትና ቅርስ የሆኑ የእምነት ተቋማትን ማቃጠል ኋላ ቀርነት በመሆኑ ህዝቡ ይህንን ለመመከት በአንድነት ሊቆም እንደሚገባም አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ በተለይ በተያዘው በጀት ዓመት የመንገድ ግንባታ ከፍተኛ በጀት እንደተያዘለትና ተጀምረው የቀሩ መንገዶች እንደሚሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በቂ ባይባልም በክልሉ በጤና በኩል ጥያቄ በተነሳባቸው ዞኖች ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል። የውሃ ችግርንም ለመፍታት እንዲሁ ሰፊ በጀት መያዙንም ጠቁመዋል።
በአሁን ወቅት መንግሥት አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን የመክፈት እቅድ እንደሌለውና የትምህርት ጥራትና የተመረቁትን ሥራ ማስያዝ ላይ አተኩሮ እንደሚሰራና ብዙ ሀብት ወደ አገር ውስጥ በማምጣት ሥራ በመፍጠር ሥራ አጥነት ለመቀነስ ትኩረት መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2012
አዲሱ ገረመው