አዲስ አበባ:- በኢትዮጵያ ግጭቶችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጠሩ ያሉት በመንግስት ሳይሆን የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ባላቸው ቡድኖችና ግለሰቦች መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ትላንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወር አፈፃፀሙን ባቀረበበት ሪፖርት ላይ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንዳሉት በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች መነሻቸው መንግስት ሳይሆን የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው።
በተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚራመዱ የፖለቲካ አስተሳሰቦች በአገሪቱ ለሚስተዋሉ አመጾችና ግጭቶች ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ያሰመሩበት ኮሚሽነሩ በተለይ የፖለቲካ ፍላጎቶች፣ ከማንነትና ከወሰን ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች፣ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች አገሪቱን ለቀውስ እንደዳረጓት ነው ብለዋል።
ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንደገለጹት፤ በሀገራችን በተጀመረው አዲስ የፖለቲካ ምእራፍ እና ሀገራዊ የለውጥ እርምጃዎች መካከል በአዲስ መልክ እንዲደራጅ የቅድሚያ ትኩረት ከተሰጣቸው የዲሞክራሲ ተቋማት አንዱ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ነው፡፡
ይህ ሊሆን የቻለው አዲሱ የፖለቲካ ምእራፍ እና ለውጡ እራሱ የተወለደው በረጅም ጊዜ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጥርቅም እና የሰብዓዊ መብቶች ትግል በመሆኑ፤ የለውጡ መሪዎችም ኃላፊነታቸውን የተረከቡት የሰብዓዊ መብቶችን ሙሉ ለሙሉ ለማክበርና ለማስከበር ቃል በመግባት ስለሆነ መሆኑን ኮሚሽነር ዳንኤል ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን ኮሚሽኑ ከተቋቋመ 15 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በፀዳ ሁኔታ ሲሰራና የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር ያልቻለ ተቋም ሆኖ የቆየ ሲሆን ይህንን አሰራር ስር ነቀልና ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ ለመቀየርና በዘላቂነት ላይ የተመሰረተ አሰራር ለመዘርጋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሽግግር ወቅት እቅድና የእለት ተእለት መደበኛ ስራዎችን ማስቀጠል የሚያስችል የበጀት ዓመቱን እቅድና መርሐ ግብር ቀርፆ እየተገበረ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ በተለይ የሽግግር ወቅት እቅዱ አጠቃላይ ግብ በጥናት ላይ የተመሰረተ መረጃ እንዲሁም በህገ-መንግሥቱና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መርሆዎች ኮሚሽኑ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ብቃት ያለው ተቋም አድርጎ በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡
ለሰብዓዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበርና መጠበቅ፤ እንዲሁም በህዝብ ዘንድ አመ ኔታና ተቀባይነት ያለው፣ ለህዝብ ተደራሽ የሆነና አገልግሎቱን በቀላልና ቀልጣፋ መንገድ የሚሰጥ፣ የሰብዓዊ መብቶችን ግንዛቤና ባህል በሁሉም ደረጃ በማስፋፋት፤ እንዲሁም የአጥፊዎችን በህግ ፊት ተጠያቂነት በማረጋገጥ ለዜጎች ሰብዓዊ መብቶች መከበር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያበረክት የሚችል ተቋም የማድረግ ሥራም እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከመዋቅር፣ የሰው ሀይል ልማትና አቅም ግንባታ፣ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ፣ ማወያየትና ስልጠና መስጠት አንስቶ በርካታ ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ባሉት ስምንት ቅርንጫፎቹ 704 አቤቱታዎችን ተቀብሎ ማስተናገዱንና ከእዚህም ውስጥ 191ዱ ተቀባይነት አግኝተው ለ22ቱ የመጀመሪያ ደረጃ መፍትሄ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ 120 ገዳዮች በምርመራ ላይ መሆናቸውንና 49ኙን ደግሞ በማስማማት ሂደት ላይ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
በቀረበው ሪፖርት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በደካማና ጠንካራ ጎኖች፤ መሻሻልና ተጠናክረው ሊቀጥሉ ስለሚገባቸው አሰራሮች አስተያየቶች ተሰጥቶባቸውና የቋሚ ኮሚቴው ግምገማ ተሰምቶ ውይይቱ ተጠናቋል።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2012
ግርማ መንግሥቴ