– የበረሃ አምበጣ ከአራት አገሮች ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ነው
አዲስ አበባ፡- በ2011/12 የምርት ዘመን አጠቃላይ 329ነጥብ3 ሚሊዬን ኩንታል ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። አሁን ላይ ከአራት አገራት በአምስት በሮች ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ያለውን የበረሃ አንበጣ መንጋ መከላከል የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑም ተጠቁሟል።
ትናንት በሚኒስቴር መስሪያቤቱ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ገርማሜ ጋሩማ እንደተናገሩት፤ በ2011/12 የምርት ዘመን 13ነጥብ7 ሚሊዬን ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን፤ እስካሁን 12 ነጥብ 34 ሚሊዬን ሄክታሩ (90 በመቶው ምርት) ተሰብስቧል። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ መሰረትም 329ነጥብ3 ሚሊዬን ኩንታል ምርት ተገኝቷል።
እንደ አቶ ገርማሜ ገለጻ፤ በምርት ዘመኑ 382 ሚሊዬን ኩንታል አጠቃላይ ምርት ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፤ ከ30ሺ ቀበሌዎች በተሰበሰበ ሪፖርት በአስተዳደራዊ መረጃ መሰረት 372ነጥብ5 ሚሊዬን ኩንታል ተገኝቷል። የማዕከላዊ ስታስቲክስ ደግሞ በ2ሺ800 ቀበሌዎች በሰበሰበው ናሙና መሰረት 329ነጥብ3 ሚሊዬን ኩንታል ስለመሆኑ አስታውቋል። በመሆኑም ሊወሰድ የሚገባውና ዓለማቀፍ ተቀባይነት ያለው የማዕከላዊ ስታስቲክስ መረጃ በመሆኑ የምርት ዘመኑ ምርት መጠን 329ነጥብ3 ሚሊዬን ኩንታል ነው። ይሄም ዓምና ከነበረው የ315ነጥብ5 ሚሊዬን ኩንታል ምርት አኳያ ሲታይ የ4ነጥብ33 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
ከዚህ በተጓዳኝ የቆላ ስንዴን የማልማት ሥራ እንዲሁም የመስኖ ልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ገርማሜ፤ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ መተካትን ታሳቢ ተደርጎ የሚከናወነው የቆላ ስንዴ ልማት ስራም በሦስት ተፋሰሶች ላይ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም በኦሞ ተፋሰስ በ2ሺ50 ሄክታር እና በዋቤ ተፋሰስ በ500 ሄክታር የሙከራ፤ በአዋሽ ተፋሰስ ደግሞ በ12ሺ ሄክታር ላይ የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁሉም ቦታዎች ስራውን ማስፋት የሚስችል አበረታች ውጤት መገኘቱን እና ከእስራኤልም ባለሙያዎች መጥተው እንደሚያግዙ የተናገሩት አቶ ገርማሜ፤ በመስኖ ልማት ሥራ ረገድም በዚህ ዓመት አንድ ነጥብ2 ሚሊዬን ሄክታር ለማልማት እየተሠራ
መሆኑንና እስካሁንም 800ሺ ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን እንዲሁም ቀድመው የተዘሩት እየተሰበሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሳላቶ እንደተናገሩት ደግሞ፤ ከሰኔ 2011 ጀምሮ ያደገ የበረሃ አምበጣ ከየመንና ከሱማሌ ላንድ ወደኢትዮጵያ ተከትሎ በወቅቱ በነበረው ምቹ የዝናብና የአፈር እርጥበት ተጠቅሞ በኢትዮጵያ እንቁላል ጥሎ ተፈልፍሏል።
በወቅቱም ወደአገር ውስጥ የገባውን አንበጣ ጉዳት እንዳያደርስ ከመከላከል ባለፈ የተፈለፈለው አንበጣም ሳያድግና የመራባት ደረጃ ላይ ሳይደርስ የማጥፋት ሰፊ ሥራ ተከናውኗል። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ከሁለት አገራት በሁለት አቅጣጫ ሲገባ የነበረው የአንበጣ መንጋ፤ አሁን ላይ ከአራት አገራት(ከሶማሌ ላንድ፣ ከፑንት ላንድ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ) በአምስት አቅጣጫ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ይገኛል።
ይሄን መንጋ ለመከላከልም እነዚህን አምስት የመግቢያ በሮች መሸፈን በሚያስችል መልኩ አራት አውሮፕላኖች ወደ ሥራ ተሰማርተዋል። የአንበጣ መንጋው መኖሩን ለማረጋገጥ በ145ሺ875 ሄክታር መሬት ላይ አሰሳ የተካሄደ ሲሆን፤ 65ሺ248 ሄክታር መሬት ላይ መከሰቱ ተለይቷል። በ58ሺ628 ሄክታር ላይም መከላከል ተችሏል። ለዚህም 37ሺ826 ሊትር ፀረ ተባይ ጥቅም ላይ ውሏል።
በእስካሁን ሂደትም በአምስት ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር የአምበጣ መንጋው የተከሰተ ሲሆን፤ በእነዚህ ውስጥ በሚገኙ 70 ወረዳዎች መንጋው ምልልስ አድርጓል። ችግሩን በቀጣይነት ለመከላከልም እንደ አገር እየተሰራ ካለው ሥራ ባለፈ አካባቢያዊ ትብብር ተፈጥሮ እየተሰራ እንደሆነ አቶ ዘብዴዎስ ተናግረዋል።
በመግለጫው ወቅት እንደተገለጸው፤ በምርት ዘመኑ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብም ሆነ የአንበጣ መንጋ በአገሪቱ በሰፊው ተከስቶ ነበር። ይሄን ክስተት ቀድሞ መረዳትና የተቀናጀ ዝግጅት ተደርጎ መከላከል ባይቻል ሙሉ ለሙሉ ሰብል ማጥፋት የሚችሉበት እድል ነበረ። ሆኖም በተሰራው የተቀናጀ ሥራ ጉዳቱን ዜሮ ማድረግ ባይቻልም ሊፈጠር የነበረውን አደጋ መከላከል ተችሏል።
በዚህም በተለይ በአንበጣ መንጋው በጥቂት የማሽላ ሰብል ማሳ ላይ ከደረሰ ጉዳት በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል ጉዳት አልደረሰም። በምርታማነት ላይም የፈጠረው ተጽዕኖም የለም። ይልቁንም በምርት ዘመኑ በማሳም ሆነ በምርት ላይ ጭማሪ ታይቷል። ይህ ደግሞ የምግብ ዋስትናን ስጋት ላይ የሚጥል ክስተት አለመኖሩን፤ ይልቁንም አስተማማኝ የምግብ ዋስትና መኖሩን ያሳያል።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2012
ወንድወሰን ሽመልስ