በፍትህ ዘርፉና በፖለቲካው መስክ በነበራቸው ቆይታ ለአቋማቸውና ላመኑበት ጉዳይ ባላቸው ቆራጥነት በፅናት ተምሳሌትነት ይቆጠራሉ፡፡ በተለይም በአገሪቱ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የመንግስትን ህፀፆች በድፍረት በመግለፅ ለዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ በከፈሉት ዋጋ ምክንያት በበርካቶች ዘንድ ትልቅ ስፍራ አሰጥቷቸዋል፡፡ ከስምንት ዓመታት የስደት ኑሮ በቅርቡ ወደአገራቸው ተመልሰዋል፡፡ የዛሬዋ እንግዳችን የቀድሞዋ የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኛ፣ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አመራርና የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ መስራችና መሪ የነበሩት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፡፡ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባሎች መስከረም ከመጥባቱ አስቀድሞ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ እርሶ ትንሽ ዘግየት ብለው ነው የመጡበት ምክንያቱ ምን ይሆን?
ወይዘሪት ብርቱካን፡- እኔ የዚህ አገር ለውጦች መታየት ከጀመሩ ወዲህ ህልጊዜ ወደዚህ መምጣት እፈልግ ነበር፡፡ ለነገሩ ከዚያም በፊት እዚህ መሆን በጣም እጓጓ ነበር፡፡ በተለይም እስረኞቹ ሲፈቱና ከዚያም ቀጥሎ የመጡ ለውጦች በሚታዩበት ጊዜ ከሰዎቹ ደስታ ጋር አብሬ ብካፈል ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ያጋጠሙን ችግሮች አሉ፡፡ እሱንም አብሬ ብካፈል ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግን ያው የቤተሰብ ሃላፊነት አለ፥ እና ልጄን የማሳድገው ብቻዬን በመሆኑ እንዲሁም ተማሪም ስለሆነች እነዚህን ማስተካከል ነበረብኝ፡፡ ልጄ የምትቆይበትን ሁኔታ የተለያዩ አማራጮችንም እያየሁ ስለነበረ ነው፡፡ ግን ያም ቢሆን ለስራ በጣም ዘገየ የሚባል አይመስለኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና አቶ ለማ መገርሳ ጋር ስታወሩ የሚያሳዩ ፎቶ ግራፎችን ተመልክተናል፡፡ እንዳው በዛ ወቅት በምን ጉዳይ ላይ ስትወያዩ እንደነበር ሊገልፁልን ይችላሉ? ምንአልባት አሁን ወደአገር ለመምጣት ምክንያት ሆኖዎት ይሆን?
ወይዘሪት ብርቱካን፡- አዎ! ብዙ ነገሮች አንስተናል እንግዲህ፡፡ መጀመሪያ ምስጋና በእኔ በኩል አቅርቤያለሁ፡፡ምክንያቱም እነሱም እንደሌሎች ታጋዮች ሁሉ ሃላፊነት ወስደው በህይወታቸውም ጭምር ይህንን ለውጥ ለማምጣት በመቻላቸው፡፡ በውስጥ ሆነው ሪፎርም ለማድረግ በመሞከራቸውና ያንን ቁርጠኝነት ወስደው ለውጥ በማምጣቸው ያለኝን አድናቆትና አክብሮትም ቸሬያለሁ፡፡
በተጨማሪም እነሱ በሚያደርጓቸው የስራ ሂደቶች ያጋጠሟቸውን ችግሮች በተመለከተ በተለይ ከፖለቲካው ጋር በተያያዘ እኔ ካለኝ ልምድ አንፃር በአቅሜ ለመምከር ሞክሬያለሁ፡፡ ይህ ማለት እነሱ አያውቁትም ማለት ሳይሆን ከውጭ ደግሞ በተለየ ሁኔታ የሚታይ ነገር ሊኖር ስለሚችል፡፡ ከዚህም ባሻገር እኔ ምን አስተዋፅኦ ላደርግ እችላለው የሚለውን የዚያን ጊዜም ተነጋግረናል፡፡ እንደጠየቅሽኝ ያን ጊዜ ያወራናቸው ነገሮች አሁን ከመምጣቴ ጋር በተወሰነ ደረጃ ይያያዛል ብዬ አምናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ባለፉት ሰባት ወራት የመጡትን ፖለቲካዊ ለውጦች በምን መልኩ ነው የሚገነዘቡት? ያሉት ተስፋዎችና ተግዳሮቶችስ?
ወይዘሪት ብርቱካን፡- ትልቁና መልካሙ ነገር ለውጡን ለማስጀመርና ለማስቀጠል ያለው ቁርጠኝነት ነው፡፡ በእርግጥ ይሄ ለውጥ በአብዛኛው ከህዝቡ ጥያቄና በህዝብ ትግል ምክንያት የመጣ እንደሆነ እረዳለሁኝ፡፡ ከውስጥ መምጣቱ የተወሰኑ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ትልልቅ ኪሳራዎችን ለመቀነስ እንደመልካም አጋጣሚ ሊቆጠር የሚችል ነው፡፡ ከዚያ በኋላም ህዝቡ ነፃነቱን ማረጋገጥ የሚችልባቸው ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ የግለሰብ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት፥ የሚዲያዎች መበራከት፥ ሙሉ ለሙሉ ባይባልም እንኳን የፖለቲካ እስረኛ አለ የምንልበት ሁኔታ አለመኖሩ በራሱ ጥሩ እድል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እሱ በትክክለኛ አቅጣጫ እየሄደ ያለ ይመስለኛል፡፡ በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ነጻ እንቅስቃሴ ለማድረግ የተሻለ ሁኔታ ላይ መሆናቸውም ተስፋ ሰጪ ነው፡፡
ከዚያ ውጭ ግን ሁላችንም እንደምና ውቀው ብዙ ግጭቶች እየመጡ ነው፡፡ እንደ ህዝብ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት በሚያስተሳስረንና በመከባበር በሚያኖረን ነገር ላይ ከተለያየ አንፃር ጥቃት እየተሰነዘረበት እንደሆነ አያለሁ፡፡ ግጭቶች እየመጡ እንደሆነ ያም ደግሞ ከህግ የበላይነት አንፃር ብዙ ሳንካ እንዳጋጠመው እሱንም እመለከታለሁ፡፡ ግን ዞሮ ዞሮ እነዚህን ተግዳሮቶችን በመቀነስ እድሎቹ የማይቀለበስ ውጤት እንዲያመጡ ለማድረግ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ይህንን ለማድረግ የሚያስችሉ ተቋማትን መገንባትና እነዚያ ተቋሞች በህግ በተቀመጠ ትክክለኛ አሰራር ላይ መታነፅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ በሙያ በታነፁና ስነ ምግባራቸውና ብቃታቸው በተመሰከረላቸው ሰዎችም መመራት ይኖርባቸዋል፡፡ በተቋማዊ አደረጃጀታቸውም ላይ አስፈላጊውን ሪፎርም ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ነገሮች በጣም አስፈላጊዎች መሆናቸውን አያለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርሶ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ብዙ ያገለገሉ እንደመሆንዎ በዋነኝነት ሊሻሻሉ ሊፈቱ ይገባቸዋል የሚሏቸው ችግሮች ምንድን ናቸው?
ወይዘሪት ብርቱካን፡- ለምሳሌ ከወንጀል ፍትህ አንፃር፥ የማረሚያ ቤት አያያዛችን መስተካከል አለበት፡፡ ይህም ይስተካከላል ስላልን ብቻ አይስተካከልም፡፡ ግልፅ የሆኑ አለምአቀፍ የአሰራር ደረጃዎችና አገር አቀፍ ህጎችም አሉ። ያንን እያንዳንዱ ተቋም በምን መልኩ እንደሚተገብር፤ ባይተገብር ደግሞ ምን ችግር እንደሚያጋጥመው የሚያስቀምጥ መመሪያ መውጣት አለበት፡፡ ለሚመለከታቸውም አካላትም ስልጠና መሰጠት አለበት፡፡ ፖሊስ ላይ ያለው ነገርም እንደዛው በጣም አንገብጋቢ ይመስለኛል፡፡ የፖሊስ ሃይሎቻችን ሰዎችን አላግባብ በመያዝና መብቶቻቸውን ባለማክበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው እስከሚያምኑበት ድረስ መንግስታዊ ሰቆቃ ወይም ቶርች በመፈፀም ላይ የተሰማሩ እንደነበሩ እናውቃለን፡፡ ይሄ አዋጅ ስለወጣ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቭዥን ስለተናገሩ ብቻ የሚቀየር ነገር አይደለም፡፡ ህጉ እንዴት ነው የሚተገበረው በሚለው ነገር ራሱ በጣም ዝርዝር ማዕቀፍ ያለው አሰራር መዘርጋት አለበት፡፡ እያንዳንዱ መርማሪ ሲመረምር ምንድነው ማድረግ ያለበት? ባያደርግ እንዴት ነው ክትትል የምናደርገው? ግልፅነት እንዴት ነው የሚኖረው? ተጠያቂነትስ እንዴት ነው የሚመጣው? ለሚለው የታወቁ የአለምአቀፍ አሰራሮች አሉ፡፡እነሱን በህግ መልክ በዝርዝር ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ በመመሪያም መደገፍ አለበት፡፡ ያ ደግሞ በአጭር ጊዜ የሚደረግ አይደለም፡፡ጥናት ለማድረግና መተግበርም ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፡፡ ግን ይሄ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ፍርድቤቶቻችንም እንደዚያው ሙያ በሌላቸው ባለሙያዎች ዳኝነት እየተመራ፤ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ባልፀዳና ቀጥታ ግንኙነት ባለው ሁኔታ እየተመራ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ከዚያም የተነሳ ህዝባዊ አመኔታንና ጥንካሬውንም አጥቷል፡፡ አሁን ተስፋ የማደርገው ያንን የሚያሻሽሉ ሁኔታ ሊመጡ ይችላሉ በሚል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀድሞ በፖለቲካው ዘርፍ ወደ ነበሮዎት ተሳትፎ ልመልሶና እንዳው ለቅንጅት መፍረስ ትክክለኛው ምክንያት ምን ነበር ብለው ያምናሉ? ተጠያቂውስ?
ወይዘሪት ብርቱካን፡- እውነት ለመናገር አሁን ይሄንን ጥያቄ ልመልስልሽ አልፈልግም፡፡ ልመልስልሽ የማልፈልገው መልስ ስለሌለኝ ወይም ደግሞ ምክንያቱን ስላማላውቀውና ስለማልችል አይደለም፡፡ ግን እስካሁንም የተነሱትን ነገሮች ሚዲያ ላይ አይቻለሁ፡፡ አሁን አገራችን ከሁላችንም አፋጣኝ ምላሽ የምትፈልግበት ወቅት ነው፤ ከዚያ ይልቅ ሌሎች በጣም አንገብጋቢ ጥያቄዎች አሉ፤ ከዚህ በፊት በነበረን ነገር ማን ጥፋተኛ ነው ፤ ማን የበላይ ነው? ማን የበታች ነው? ማንነው ያፈረሰው? ለምን ፈረሰ? የሚለውን ነገር እርግጠኛ ነኝ የአካዳሚክ ጥናትም ለሚያደርጉ ሰዎች በጣም ጥሩ የጥናት መስክ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን እኔ በዚያ ንትርክ ላይ የመሰማራት ፍላጎትም የለኝም፡፡ ለህብረተ ሰባችንም ዋና ጉዳይ ነው ብዬ አልወስደውም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ጋር ተያይዞ ህዝቡን በሁለት ፅንፍ የሚወጥሩ አስተሳሰቦች ጎልተው እየወጡ ነው፡፡ ይኸውም የዘር ፖለቲካና የዜግነት ፖለቲካ የሚሉ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት ምልከታ ምንድነው?
ወይዘሪት ብርቱካን፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም በጣም ማስመር የምፈልገው ነገር የሃሳብ ልዩነት መቼም የሚቀር ነገር አይደለም፤ ግን እነዚያን ልዩነቶች የሚዳኙ አሰራሮችና ተቋሞች መኖር አለባቸው፡፡ የሚዳኙ ማለት ለህዝብ ፍርድ ቀርበው የትኛው ሃሳብ የተሻለ ገዢ ሃሳብ ነው? የሚለውን በህግ አግባብ የምናይበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ በየትኛውም አገር ምርጫ የሚካሄደው ገዢውን አስተሳሰብ ለመለየት ነው፡፡ የሃሳብ ልዩነት መቼም ሊጠፋ አይችልም፡፡ ልዩነቶቹ በሚኖሩበት ጊዜ አንደኛው የሌላኛውን ሃሳብ በማክበር አንድ ላይ እንደሚኖር ማህበረሰብ ደግሞ አብሮ መኖር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መግባባት መፍጠር ይገባናል፡፡አንዱ የመኖር መብት እንዳለው ሁሉ ሌላውም የመኖር መብት እንዳለው መገንዘብ ይገባል፡፡ የራስን ሃሳብ ማሳወቅ እንዳለ ሁሉ፤ ያኛውም ሃሳቡን የሚሰነዝረው እውነተኛና ትክክለኛ ነው ብሎ ስለሚያምንበት እንጂ ህዝብ ወይም አገር ለማጥፋት እንዳልሆነ መረዳት ይገባል፡፡ ልዩነቶች ከተለያየ እይታዎች ሊመጡ እንደሚችሉ፤ አንዳችንንም በሌላው ጫማ የማየትንም ነገር አብሮ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲከኞችም ለተከታዮቻቸው ያንን ማሳየት እንደሚኖርባቸውና በዚህ ውስጥ በጣም በጥንቃቄ ማለፍ እንደሚገባ ነው የምረዳው፡፡
ግጭቶች ወይም ልዩነቶች ሲፈጠሩ ደግሞ ያሉት ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት ቶሎ ቶሎ የሚገቡበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ግጭቶች ከመምጣታቸውም በፊት የሚወገዱበትንና መፍትሄ የሚሰጥበትን መንገድም ማየት ይኖርብናል፡፡ በነገራችን ላይ ወደፊትም ቢሆን እኔ ልዩነቱ ይቀራል ብዬ አላምንም፡፡ ዛሬ በፌዴራሊዝም ስርዓቱ ላይ እንከራከራለን፤ ነገ ደግሞ በሌላ ጉዳይ የምንከራከር ይሆናል፡፡ ምናልባት በቀጣይ በኢኮኖሚው ሁኔታ ወይም በድህነት የመኖሩ ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ስለመሆኑ እያነሳን እንከራከራከለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ግን ቀድም ብዬ የገለፅኳቸው ጉዳዮች ማለትም አንዱ የሌላውን ሃሳብ ማክበር፤ አንዱ ሌላውን ለመረዳት መሞከርና ህግን እያከበሩ ሃሳብን መግለፅ እንዲሁም ለተቋማት ዳኝነት መገዛት በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ካነሱት አይቀር፤ አንዳንድ ግለሰቦች አሁን ለተፈጠረው የብሄር ግጭት የዳረገን የፌዴራሊዝም ስርዓቱ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ እርስዎ በእዚህ ላይ የሚሰጡት አስተያየት ምንድነው? አሁን ለአገሪቱ የሚያስፈልጋትና ብዝሃነቷን ጠብቃ እንደአገር ለመቀጠል የሚያስችላት ፍቱን መድሃኒት ነው የሚሉት ስርዓት ካለም እግረመንገድዎን ይጥቀሱል?
ወይዘሪት ብርቱካን፡- እውነት ለመናገር ይሄ በብዙ አመታት ሂደት ውስጥ እየተወሳሰበ ያየነው ጉዳይ ነው፡፡ እኔ መፍትሄ ብዬ የማስበውን ነገር ልናገር እችላለሁ፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ ብዙ ሃሳቦችን ይዘው ሊመጡና በአንክሮ ሊከራከሩባቸው የሚችሉባቸው ነጥቦችና ሃሳቦች ይኖራሉ ብዬ አምናለው፡፡ ግን እኔ የሚታየኝ አንድ ወገን ይሄ ነው ትክክለኛው ስላለ ብቻ ለመተግበር የምንወጣበት ነገር ያለ አይመስለኝም፤ ቅድም እንዳልኩት የሌላኛውን አስተሳሰብ ማየት ይገባል፡፡ አብረን ከመኖር ልናመልጥ የምንችለው ነገር አይደለም፡፡ አንደኛው ሌላኛው ላይ የራሱን ነገር ብቻ ጭኖበት ሊኖር የሚችል ጤናማ አኗኗርና ህብረተሰብ ያለ አይመስለኝም፡፡
ስለዚህ ተሳታፊ የፖለቲካ ሃይሎች፣ መንግስትም ሆነ የሲቪክ ማህበራት እነዚህን ጫፍና ጫፍ የያዙ አመለካከቶችን ሁሉንም በሚያቅፍ፥ በተወሰነ ደረጃ በሚያቻችል፥አንዱ የተወሰነ ነገር ሰጥቶ የተወሰነ ነገር ተቀብሎ ወደፊት የሚሄድበትን ነገር መፈለግ ያለባቸውይመስለኛል፡፡ መልሱ ይሄ ነው ተብሎም መልሱ ግን እንደዚያ ላይሆን ይችላል፡፡ መልሱ ይሄነው ተብሎና ተተግብሮም ችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄ አገኙ የምንልባቸው ሊሆኑ ስለማይችሉ እኔ ወደዚያ ክርክር ገብቼ በዚህ ጋር ነው፤ በዚያ ጋር ነው ማለት አልችልም፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች እዛ ላይ ያላቸውን አቋም በግልፅ ያስቀምጣሉ፤ ተገቢም ነው፤ ግን እንደማህበረሰብ እንደሃገር ከምንም በላይ ተቻችለን የሁላችንን ሃሳብ አገራችን በምንላት በአንድ ቤታችን ውስጥ ተንፀባርቆ እንድንቀጥል ቁርጠኞች መሆን አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ አንድ ላይ መዋሃድ ትንሽ መጎዳትን፤ ትንሽ ትንሽ መስጠትንና ትንሽ ትንሽ መቀበልን ይጠይቃል ብዬ ነው የማምነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአገራችን የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚቀሩ የቤት ስራዎች ምንድን ናቸው ብለው ያምናሉ?
ወይዘሪት ብርቱካን፡- እውነት ለመናገር እከሌ ይህንን ማድረግ አለበት፤ እከሌ ደግሞ ያንን ያድርግ ብዬ መመሪያ መስጠት አልችልም፡፡ ግን ዞሮ ዞሮ በየመስኩና በየግንባሩ ባሉት ተግዳሮቶች ዙሪያ አብሮ መነጋገርና መተጋገዝን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ ተቃዋሚዎች መንግስት ይህንን አጉድሎብን ነበር ሁልጊዜ ክርክራችን፡፡ መንግስት በኛ ላይ የሚያደርገውን ጥቃት ማሳየት ነበር ዋና ስራችን፡፡ ምክንያቱም መንግስት ለእኛ እሮሮም ሆነ ለደረሰብን ችግር የሚሰጠው ምላሽ ሆን ብሎና ያሉትን የመንግስት ተቋማት በሙሉ በመጠቀም ጥቃቱን ማጠናከር ስለነበር ሁልጊዜ የምንከራከረው በዚህ ዙሪያ ነበር፡፡ አሁን ግን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጆሮም የሚሰጥ መንግስት አለ፡፡
በመሆኑም ያሉት ችግሮች መተጋገዝን መነጋገርን የሚጠይቁ ስለሆኑ አንድ ላይ መምጣትን ሃሳብ መለዋወጥንና አንደኛው ከሌላኛው ምን እንደሚጠብቅ አንደኛው ለሌላኛው ምን ማገዝ እንዳለበት ቁጭ ብለን የምንመካከርበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ መንግስትም ፓርቲዎቹ የተለያዩ አቋም ሊኖራቸው ይችላል። ግን ይህንን የሚያደርጉት በአንድ መስክ ላይ በመሆኑ እግር መረጋገጥ እንዳይኖር ምንድነው መደረግ ያለበት በሚለው ነገር ላይ ከእነሱም ጋር እየተነጋገረ በግልፅ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ግርታዎች አሉ፡፡ በጣም ጨቋኝ ከሆነ ነገር ውስጥ ስለመጣን አሁን ሁሉ ነገር ነጻና ምንም ወሰን የሌለው የማስመሰል ነገር አለ፡፡ እንደሱ የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ምንም ገደብ የሌለው ነፃነት ሊኖርም አይችልም፡፡ ስለዚህ መፍትሄው አንድ ላይ እየተነጋገሩ ህጎቹ መውጣት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ባቀረበው ጥሪ መሰረት በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎች ሳይቀር ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሃገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ምንም እንኳ ሲገቡ በሰላም ለመንቀሳቀስ ተስማምተው ቢሆንም አንዳንዶቹ አሁንም ትጥቃቸውን ያልፈቱበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ ይህ ወደፊት እንገነባታለን ለምንላት አገር ምን አይነት አሉታዊ ሚና ይኖረዋል ብለው ያምናሉ?
ወይዘሪት ብርቱካን፡- እኔ እዚያ ላይ ሁለት ነገር ነው ማለት የምፈልገው፡፡ አንዱ የህግ የበላይነት መከበር አለበት ምክንያቱም ህግ ያልተከበረበት አገር አገር ሆኖ ሊቀጥል አይችልም፡፡ የህግ የበላይነት ከሌለ ሁሉም እያዘዘ የሚኖርበት ስርዓት ይፈጠራል፡፡ ወደዚያ ደግሞ ማንም መግባት ይፈልጋል ብዬ አላምንም፤ መንግስትን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ዜጎችም ሆኑ ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች ከህግ ስር መሆንና ህግን ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይሄ ምንም ማብራሪያ የሚሻው ነገር አይደለም፡፡ ግን ሌላው ቀርቶ ከአብዮቱ ጀምሮ የነበረውን ሂደት ስንመለከተው ብዙ ትምህርቶችን መውሰድ እንችላለን፡፡ ይህም በሃይልና ጠብመንጃ የሚመጣ ነገር የትም እንደማያደርሰን ነው፡፡ ስለሆነም ፖለቲካችንን ከዚያ ለማፋታት በጣም የሰለጠነ ውይይትና ክርክር ወደማድረግ ወደዚያ ለመወሰድ መሞከር አለብን፡፡ ምክንያቱም ብዙ የሚጠበቅብን የቤት ስራ አለና፡፡ እያንዳንዳችንም እንደዜጋ ከግጭት መሸሽ፣ ሁልጊዜ የሃሳብ ክርክርን የሃሳብ መግባባትና የመቻቻል ባህል ማዳበር ይገባናል፡፡ የሚጠቅመንም እሱ ብቻ ስለሆነ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብርቱካን የሚለው ስም ሲነሳ በርከት ያሉ ሰዎች ላመኑበት ነገር ባሎዎት ቁርጠኝነት የፅናት ተምሳሌት አድርገው ይወስዶታል፡፡ ለመሆኑ የዚህ ፅናት ሚስጥር ምን ይሆን?
ወይዘሪት ብርቱካን፡- እንግዲህ የፅናትን ነገር ካነሳን እኔ የተለየ ፅናት አለኝ ብዬ አልቆጥርም፡፡ እስካሁን አቅም ሆኖ ያስቀጠለኝ ነገር የቆምንላቸውና በአገራችን ላይ ልናያቸው ለፈለግናቸው ነገሮች ያለኝ ፍቅር ነው፡፡ በተጨማሪ ለምኖርበት ማህበረሰብ፥ ለዜጎችና ለወገኔ ያለኝ ፍቅር ነው፡፡ እሱ በፅናት እንድቀጥል ያደርገኛል፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን እኔ የተለየ ብርታት ወይም ጥንካሬ አለኝ ብዬ አላስብም፡፡ ግን የነበርኩበት የስራ መስክ ላይ ብዙ ሴቶች የማይታዩ ስለሆኑ እንደተለየ ነገር መቆጠር ያጋጥማል፡፡ ለምሳሌ ብጠቅስልሽ ዳኛ በነበርኩበት ጊዜ የማስታውሰው ነገር ጥቂት ዳኞች በመሆናችን ብቻ ሰዎች ይመጡና «ሴቷ ዳኛ ናት እንዲህ ያለችኝ» ይላሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ጥቂት መሆናችን ብቻ ነው፡፡ ያ በመሆኑ በጣም አዝናለሁ፡፡ ግን አሁን እየተለወጠ መሆኑ መልካም ነገር ነው፡፡ አንድ ሆኖ መታየት ሳይሆን ብዙም እኩልም ሆነን በዚህ መስክ መሰማራታችን እንደተፈጥሯዊ ነገር እና እንደተለመደ ነገር መወሰድ አለበት፡፡ በሴቶች በኩል የሚመጣውን ምልከታና የተለየ አይነት አስተዋፅኦ የማይቀበል ማህበረሰብ ራሱን ነው የሚጎዳው፡፡
እኔ በዳኝነት በምሰራበት ጊዜ የእኔን ጉዳይ እንደልዩ ፅናት አላየውም፡፡ ዳኝነት የተከበረ ስራ ነው፡፡ ምንም እንኳ ደመወዛችን አነስተኛ ቢሆንም በከፍተኛ ፍቅር ነበር ስንሰራ የነበረው፡፡ ወድጄው እሰራ ስለነበር ነው ብዙ ሰዎች የፅናት ተምሳሌት አድርገው የሚስሉኝ፡፡ ለሙያው ተገዢ ካልሆንኩ ደግሞ ዝም ብዬ ህይወቴን ማልከስከስ አድርጌ ነበር የምቆጥረው፡፡ በምንወስናቸው ነገሮች ተቃራኒውን ወይም ያልሆነ ነገር እንድንወስን እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ተፅእኖ ይደርስብን ነበር፡፡ በፖለቲካ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ያንንን የፖለቲካ ተፅእኖ አልፎ የማይሆን ውሳኔ መስጠት አዕምሮዬ ውስጥ አልመጣም አልልሽም፡፡ ግን ትክክል ያልሆነ ውሳኔ ወስኜ ዝም ብዬ ዘልዓለም ህሊናዬን ሲያሳክከኝ ከምኖር ትክክለኛውን ወስኜ የሚመጣውን ለመቀበል የምቆርጥባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ እንዳልኩሽ ሙያውም የተከበረ ነው፤ እኔ ደግሞ ትራፊም ህይወት የለኝም ፡፡ ስለዚህ እኔ በማምንበት መንገድ ትክክል ነው ብዬ ያመንኩትን አደርጋለው፡፡ ብዙ ሰዎችም እንደዚያ ያደርጋሉ፤ የኔ የተለየ ነው ብዬ አላስብም፤ ምንአልባት ያለው ችግር የተለየ አስመሰለው እንጂ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅርቡ በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይ ታወቅበት ሁኔታ ሴቶች ከወንዶቹ እኩል ትላልቅ የሚባሉትን መንግስታዊ ስልጣኖች እንዲጋሩ ተደርጓል፡፡ ይህንን ሁኔታ በርካቶች ቢደግፉትም አንዳንዶች ግን ከብቃት አኳያ ሴቶቹ የወንዶቹን ያህል አይመሩም ወይም አይሰሩም የሚል ጥርጣሬ አላቸው፡፡ በዚህ ላይ የሚሰጡት አስተያየት ይኖር ይሆን
ወይዘሪት ብርቱካን፡- እኔ በተወሰነ ደረጃ ብዙ ሴቶች ከተሾሙ በኋላ ውይይቱን ለመመልከት ሞክሪያለው፤ እና ትንሽ ገርሞኛል፡፡ ምክንያቱ ከእነሱ እኩል የተሾሙ ወንዶችም አሉ እና አንዳንድ ጊዜ ስለ ወንዶቹ ብቃት ምንም ሳይባል ሴቶቹ ላይ ብቃት አለ፤ የለም፤ የሚል ክርክር ይነሳል፡፡ በእኔ አመለካከት እስካሁንም ወደኋላ ያስቀረን አንዱ ነገር ይሄ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በሁለት ሚዛን የመመዘን ነገር አያለሁ፡፡ ታውቆም፤ ሳይታወቅም ማለት ነው፡፡ ሴቶች ጋር ሲመጣ አይ ብቁ የሆኑ ሴቶች ስለሌሉ ነው ይባላል፡፡ ግን እድሉ ካልተሰጣቸው መታየቱም እድል አይኖርም፡፡ እኔ አሁን የተሾሙት ሴቶች ብዙ ነገር እንደሚያሳኩ እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባሉበት ሁኔታ አገርዎን በምን ዘርፍ ነው ማገልገል የሚፈልጉት?
ወይዘሪት ብርቱካን፡- ለብዙ ጋዜጠኞች ይህንን ጠቅሼዋለሁ፡፡ እንግዲህ ትምህርቴም ሆነ ልምዴ የተያያዘው ከህግ፥ ከፖሊሲና ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር የተሳሰረ ስለሆነ ከእነዚያ ጋር በተያያዘ የተሻለ ነገር ለመስራት የምችልበትን ነገር እያየሁኝ ነው፡፡ ከዚያ ጋር በተያያዘ ጥሩ ነው ብዬ በማምነው ዘርፍ በቅርቡ ብቅ እላለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የምርጫ ቦርዱ ጉዳይስ?
ወይዘሪት ብርቱካን፡- እሱን አሁን አዎም፤ አይም፤ ልልሽ አልችልም፡፡ ምክንያቱም በቂ መረጃ የለኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ያሎዎትን ጊዜ አጣበው ለቃለ መጠይቁ ስለተባበሩኝ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ወይዘሪት ብርቱካን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ማህሌት አብዱል