ጎንደር፦ በጎንደር የጥምቀት በዓል ላይ የእንጨት ርብራብ መቀመጫ ተደርምሶ በደረሰባቸው አደጋ ህይወታቸውን ለማትረፍ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በተደረገላቸው ህክምና መደሰታቸውን ተጎጂዎች ተናገሩ።
ተጎጂዎቹ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ አደጋው ከደረሰባቸው ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን በሆስፒታሉ እየተደረገላቸው ያለው ህክምናና እንክብካቤ እንዳስደሰታቸው ገልፀው፤ በዚህም የበርካቶችን ህይወት ማትረፍ መቻሉን ተናግረ ዋል።
በጎንደር ዩኒቨርስቲ አራተኛ አመት የላቦራቶሪ ተማሪ ዘላለም አዳሙ መቀመጫ ቦታው ከመጠን በላይ ሰው በማስተናገዱ መደርመሱን ገልፆ፤ በደረሰበት ጉዳት ህክምና ውን ተኝቶ እየተከታተለ ሲሆን ከመጀመሪያ ህክምና ጀምሮ እየተደረገለት ባለው እርዳታ ህይወቱ መትረፉን አብራርቷል።
የደረሰው አደጋ አሰቃቂ የነበረ ቢሆንም የህክምና ባለሙያዎች ባደረጉት ርብርብ የብዙ ተጎጂዎችን ህይወት መትረፍ ችሏል፤ በዚህም ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ሌላኛዋ ተጎጂ ትብለጥ ቢወጣ በበኩሏ በደረሰባት አደጋ ወደ ሆስፒታሉ ከገባችበት ጊዜ አንስቶ እየተደረገላት ያለው የህክምና እርዳታ የባለሙያዎችን ስነምግባራዊ አገልግሎት ያስተ ዋለችበትና የበርካቶችን ህይወት ማትረፍ የተቻለበት እንደሆነ ገልፃለች።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታልና የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበው የህክምና ባለሙያዎቹ ከቤታቸው ጭምር ወደ ሆስፒታሉ በመሄድ ተጎጅዎችን ተረባርበው ማከማቸውን ገልፀው፤ መሰል ስራ ባይሰራ ኖሮ የሟቾች ቁጥር ይጨ ምር ነበር ብለዋል።
ሆስፒታሉ መረጃው ከደረሰው ሰዓት ጀምሮ ከፍተኛ ክትትልና ርብርብ በማድረግ 250 የሚሆኑ ተጎጂዎችን ማስተናገዱን የገለፁት ዶክተር አሸናፊ 7 ግለሰቦች ሆስፒታል እንደደረሱ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን 2 ግለሰቦች ደግሞ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው በነበረበት ወቅት መሞታቸውን ተናግረዋል፤ ከሟቾች ውስጥም ሁለቱ ሴቶች ናቸው።
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በሆስፒታሉ 80 ሰዎች ተኝተው እየታከሙ ሲሆን 2 ታካሚዎችን ለተሻለ ህክምና ወደ አዲስ አበባ ለመላክ ሆስፒታሉ ዝግጅት ማጠናቀቁን ስራአስፈፃሚው ገልፀዋል።
የ2 ጉዳተኞች ህይወታቸው አስጊ ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ በፅኑ ህሙማን ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ ቀላል ጉዳት ያጋጠማቸው ግለሰቦች ህክምና እያገኙ ወደቤታቸው መመለሳቸውን ሰምተናል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር አያሌው ተክሉ በበኩላቸው በበአሉ አከባበር ጠዋት ላይ በተከሰተው አደጋ የ10 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን አንድ ሞት የተመዘገበው ከሆስፒታል ውጪ መሆኑን ገልፀዋል።
13 ተጎጂዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ ባቸው የገለፁት ኮማንደር አያሌው 4 የክ ልሉ አድማ ብተና ፖሊስ አባላትም ጉዳት እንደደረ ሰባቸው አስረድተዋል፤ አጠቃላይ የድርጊቱን አፈፃፀም እና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ፖሊስ የማጣራት ስራ እየሰራ መሆኑንም ተናግረ ዋል።
ኮማንደር አያሌው አያይዘውም የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር መጠናቀቁን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2012
ድልነሳው ምንውየለት