ጎንደር:- በጥምቀት በዓል በወጣቶች ዘንድ የታየው የአንድነትና አብሮነት መንፈስ የዘወትር ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ወጣቶች ገለፁ።
1982ኛው የእየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል መታሰቢያ ትናንት በሀገር አቀፍ ደረጃ በጎንደር ከተማ በተከበረበት ወቅት አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰጡ ወጣት ምዕመናን በአሉ የደመቀ፣ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ወጣቶች በአንድነትና አብሮነት መንፈስ ሲንቀሳቀሱ ማየታቸውን ገልፀዋል።በመላ ኢትዮጵያ ጥምቀት ባማረ መልኩ እንዲከበር ትልቅ ድርሻ የወሰዱት ወጣቶች ሀገራዊ አንድነታቸውን በማረጋገጥ በኩልም ጠንክረው እንዲንቀሳቀሱ አስተያየት ሰጪዎቹ መክረዋል።
በጎንደር ከተማ በግንባታ ሰራተኝነት የተሰማራው ወጣት እንዳዩ መልካም,በአሉ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ብሎም በሰላም እንዲጠናቀቅ ወጣቶች ያደረጉትን ርብርብ አድንቆ አሁን በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄው ያለው በዚህ ትውልድ እጅ በመሆኑ ቆም ብሎ ማሰብና ማስተዋል እንደሚጠበቅበት ተናግሯል።
ወጣት እንዳዩ በመልዕክቱ ሀገር የምትሰራውም ሆነ የምትፈርሰው በወጣቱ ሀይል በመሆኑ የጥፋት መንገድን በመሸሽ ለጋራ ብልፅግና በአብሮነት መቆም ከወጣቱ እንደሚጠበቅ ገልጿል።
በዓላት የአንድነት መገለጫዎች በመሆናቸው በእነዚህ ወቅቶች የሚስተዋልን ትብብር በዘወትራዊ እንቅስቃሴም አስጠብቆ ማስቀጠል እንደሚገባ የገለፀችው ደግሞ ጥምቀትን በጎንደር ለመታደም ከአዲስ አበባ የመጣችው ወጣት ኤደን ሀይለሚካኤል ናት።
እንደ ወጣቷ ገለፃ አሁን ላይ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች በተለይም የዩኒቨርስቲ ወጣት ተማሪዎች ነገሮችን ቆም ብሎ ካለማገናዘብ የመነጩ በመሆናቸው ችግሩን ለመቅረፍ በበዓላት ወቅት የሚፈጠሩ መናበቦችን በእለት ከእለት እንቅስቃሴ መድገም ይገባል።
ወጣት ዲያቆን ዮሴፍ ደሳለው ደግሞ የእያንዳንዱ ወጣት እንቅስቃሴ የፈጣሪን ህግ በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት በመግለፅ እየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሀንስ ለመጠመቅ ጥያቄ ባቀረበለት ጊዜ ዮሀንስ ያሳየውን ትህትና እና ጌታም ዝቅ ብሎ የተጠመቀበት ምስጢር ለወጣቶች ትልቅ ተምሳሌት ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል።
ወጣቶች በባህረ ጥምቀቱ ግቢ ውስጥ ምዕመናንን ተሸክሞ የነበረው የእንጨት ማማ በተደረመሰበት ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን ወደ ህክምና በመውሰድና በከፍተኛ ርብርብ ለሰሩት የነፍስ ማዳን ስራ አስተያየት ሰጪዎቹ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አራተኛው የቤተክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ በአሉን የታደሙ ሲሆን አቡነ መርቆርዮስ ከ30 አመታት በኋላ ጥምቀትን ለመጀመሪያ ጊዜ በጎንደር ስለማክበራቸው ተገልጿል።
በበዓሉ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ፣ ቀዳማይ እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም እና ከፍተኛ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
ጥምቀት ባለፈው ታህሳስ ወር በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ የማይዳሰስ የአለም ቅርስነት በተመዘገበ ማግስት ትናንት በመላ ኢትዮጵያ የተከበረ ሲሆን በጎንደርም በርካታ የውጪና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ጨምሮ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2012
ድልነሳ ምንውየለት