ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ጀርባ ይገኛል። በዘመነ አጼ ኃይለስላሴ የመጀመሪያውና ፈር ቀዳጁ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት እንደሆነ ይነገርለታል። የዘውዳዊው ስርአት ማክተሙን ተከትሎ ታዲያ የካቲት 12 በሚል ስያሜ የሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት በመሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አገልግሏል።
ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ወቅት ወደ ቀድሞው ማንነቱ ተመልሷል። የእቴጌ መነን ሁለተኛ ደረጃ የልጅ አገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት በሚል በተያዘው በጀት አመት በአዳሪ ትምህርት ቤትነት ልጃገረዶችን ተቀብሎ ማስተማር ጀምሯል።
ምህረት ሃብታሙ በአዳሪ ትምህርት ቤቱ የአስራ አንደኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ናት።በታህሳስ ወር አጋማሽ ላይ ወደ ትምህርት ቤቱ በመምጣት ትምህርቷን መከታተል እንደ ጀመረች ታስታውሳለች። ትምህርት ቤቱ ዳግም አዳሪ ትምሀርት ቤት ተደርጎ የዚሁ እድል ተጠቃሚ በመሆኗም ደስተኛ ናት። ከአስተማሪዎቿ የተሻለ ድጋፍ ማግኘቷን ትልቅ ቦታ እንደምትሰጠው ትናገራለች።
‹‹በአዳሪ ትምህርት ቤቱ አብዛኛዎቹ ለተ ማሪ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ ተሟልተዋል›› የምትለው ተማሪ ምህረት፤ የቤተ ሙከራና የአይ ሲ ቲ ክፍሎች ቢጠናከሩ ትምህርቱን በተግባር ጭምር በመማር የተሻለ እውቀት ማግኘት ይቻላል ትላለች። ከመደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ባሻገርም በትርፍ ጊዜዋ ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ታጠናለች፤በስነፅሁፍና የኪነጥበብ ስራዎች ውስጥ አብረው ይሳተፋሉ።በማታው ክፍለ ጊዜም እንደምታጠና ታስረዳለች።
ወይዘሮ ጥሩቀለም ይስራው በአዳሪ ትምህርት ቤቱ የዘጠነኛ ክፍል የአማርኛ መምህር ናቸው። የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ከብዙ አመታት በኋላ ዳግም ተከፍቶ አገልግሎት በመስጠቱና የዚሁ አጋጣሚ ዕድል ተጋሪ በመሆናቸው በእጅጉ ተደስተዋል።
ተማሪዎቹ ከየትምህርት ቤቱ የተሻለ ውጤት አስመዝግበው የመጡና የተሻለ ስነምግባር ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ይህም ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል እድል እንደሚሰጣቸው ይጠቁማሉ። ምንም አይነት የቤት ውስጥ ጫና የሌለባቸው መሆናቸውና ሌላ የሚያታልላቸው ጉዳይ ባለመኖሩም ሙሉ ጊዜያቸውን በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ እንደሚያደርጋቸውም ይናገራሉ።
የተማሪዎቹ የክፍል እንቅስቃሴም ጥሩ መሆኑንም መምህርቷ ገልፀው፤ እያንዳንዱን ነገር በጥንቃቄ በመመርመርና በመፈተሽ እንደ ሚሰሩ፣ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበትም ወቅት ማብራሪያዎችን በጥልቀት እንደሚሰጡ፣ ስነምግባር በተሞላበት መልኩም ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ፣ ያልገባቸውን እንደሚጠይቁና በክፍል ውስጥ በንቃት እንደሚሳተፉ ያብራራሉ።
‹‹የተማሪዎቹ በሚገባ ትምህርታቸውን መከታ ተል ሃገሪቱ ተተኪ ዜጋ ለማፍራት ያላትን ተስፋ ያሳያል›› ይላሉ። በቀጣይም መንግስት ለአዳሪ ትምህርት ቤቶች ትኩረት በመስጠትና በሌሎች አካባቢዎችም እንዲስፋፉ በማድረግ ሴት ተማሪዎች የሚማሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባው ያመለክታሉ።
የትምህርት ቤቱ አስተዳደርና ፋይናንስ ምክትል ርእሰ መምህር ወይዘሮ ትእግስት ዮሴፍ በበኩላቸው እንደሚሉት፤አዳሪ ትምህርት ቤቱ ዳግም መጀመሩ ወላጆችን፣ተማሪዎችንና አጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰቡን አስደስቷል። በቅርቡም አርባ ሁለት መምህራንን፣ አራት ርዕሳነ መምህራንና የቀድሞው የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ሰራተኞችን በመያዝ ስራውን ጀምሯል። ምክትል ርእሰ መምህሯ የከተማ አስተዳደሩ 500 ሴት ተማሪዎች በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ አቅዶ እንደነበር አስታውሰው፣ባስቀመጠው የመመልመያ መስፈርት መሰረት ለጊዜው 400ዎቹን በመቀበል እያስተማረ ይገኛል ይላሉ።
የስምንተኛ ክፍል የሚኒስትሪ ውጤት፣ የክፍል ደረጃ ውጤት፣ የክፍል አማካይ ውጤትና የአስረኛ ክፍል የማትሪክ ውጤት ከመመዘኛ መስፈርቶቹ ውስጥ ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ እነዚህን መስፈርት ያሟሉ ተማሪዎች ወደ አዳሪ ትምህረት ቤቱ እንዲገቡ መደረጉን ያብራራሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤በተመሳሳይም መምህራንና ርእሳነ መምህራን የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤታቸው፣ የመመረቂያ ፅሁፋቸው ደረጃ እና የመመረቂያ ነጥባቸው የታየ ሲሆን፣የመግቢያ ፈተናውን ያለፉና በአዲስ አበባ ደረጃ ተወዳድረው መስፈርቱን ያሟሉ እንዲገቡ ተደርጓል።
ትምህርት ቤቱን መልሶ አዳሪ ትምህርት ቤት በማድረግ በኩል መሰረተ ልማቶችን በበቂ ሁኔታ ከማሟላት አኳያ ከጥቃቅን ነገሮች ውጪ የገጠሙ ችግሮች እንደሌሉም ጠቅሰው፣በትምህርት ቤቱ ውስጥም ሁለት የመመገቢያ አዳራሾች፣ አንድ ማብሰያ ክፍል፣ አምስት የማደሪያ ብሎኮችና አንድ ባለአራት ፎቅ የመማሪያ ህንፃ በበቂ ሁኔታ ተሟልተዋል ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ ምክትል ርእሰ መምህርቷ ገለጻ፤ የተማሪዎቹን ጤና ከማስጠበቅ አኳያም የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ በግቢው ውስጥ ጤና ጣቢያ ተቋቁሟል። ይሁንና ከአቅም በላይ የሆኑ የጤና ችግሮች ቢያጋጥሙ በአቅራቢያ ከሚገኝ የሽሮ ሜዳ ጤና ጣቢያ ጋር ስምምነት ተደርጓል። ደረጃውን የጠበቀ ቤተመፅሃፍትም አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ከርእሳነ መምህራን ጋር በመወያየትም መፅሃፍቶችን ከቤተመፅሃፍት ባለሞያዎቹ ጋር ርክክብ በማድረግ ተማሪዎች በማታውም ክፍለ ጊዜ ቤተመፅሃፍቱን እንዲገለገሉበት ተደርጓል።
የትምህርት አሰጣጡ በአብዛኛው የተመረጠ ነው የሚሉት ምክትል ርእሰ መምህሯ፤ ‹‹ከመደበኛው ትምህርት ያን ያህል የተለየ ባይሆንም ነባራዊ ሁኔታው ግን ሙሉ አዳር በትምህርት ቤቱ ውስጥ በመሆኑ ለተማሪዎቹ ሰፊ የማጥኛ ሰአት ይኖራቸዋል።››ይላሉ።ያለምንም እንግልት፣ ስራና ሃሳብ ነፃ ሆነው ትምህርታቸው ላይ ብቻ በማተኮር እንደሚማሩ ይገልጻሉ።
እንደ ምክትል ርእሰ መምህርቷ ወይዘሮ ትእግስት ማብራሪያ፤ትምህርቱ ከሰኞ አስከ አርብ የሚሰጥ ሲሆን፣ቅዳሜ ግማሽ ቀን በማጠናከሪያ የሚሰጥበት ሂደት ላይ ይገኛል። ለጊዜው ግን ቅዳሜ ከሰአት ማታ ሁል ጊዜ ለአንድ ሰአት ያህል ተማሪዎች በሚያዘጋጁት የምሽት ፕሮግራም ሁሉም የየራሳቸውን ተሰጥኦ ያሳያሉ። ይህም ራሳቸውን የሚገልፁበት ፣በራስ መተማመናቸውን የሚያዳብሩበት፣ እርስ በርስ የሚተዋወቁበትና የነገ እጣ ፈንታቸውን የሚያስቀምጡበት ይሆናል።
ተማሪዎቹ ቅዳሜ ከዘጠኝ ሰአት ተኩል በኋላ በወር አንድ ጊዜ ከወላጆቻው ጋር እንዲገናኙ ይደረጋል ይላሉ። በማግስቱም እስከ ስድስት ሰአት ድረስ ወደ ትምህርት ቤታቸው እንደሚመለሱ፣በእሁዱ ክፍለ ጊዜ ደግሞ ከትምህርት ነፃ ስለሚሆኑ ከጥዋት አስከ ምሳ ሰአት ድረስ ልብሶቻቸውን፣ ክፍሎቻቸውንና ራሳቸውን ንጽህና እንደሚጠበቁ ያብራራሉ። በከሰአቱ ክፍለ ጊዜም የስፖርት ጊዜ ይኖራቸዋል፤በዶርማቸው የእርስበርስ ትውውቅ ያደርጉና የሳምንቱ ክፍለ ጊዜ ይጠናቀቃል።
በቀጣይም የወላጆችን ፍቃድ በመጠየቅና በትምህርት ቤቱ ውሳኔ መሰረት የጉብኝት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ተማሪዎቹ ተዝናንተው የሚመለሱበትን ፕሮግራም ለመጀመር በእቅድ ተይዟል።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2012
አስናቀ ፀጋዬ