አዲስ አበባ፣ ባለፉት አምስት አመታት 560 የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያውያንና በተለያዩ አገራት የውጭ ባለሃብቶች ሽርክና (ጆይንት ቬንቸር) መተግበራቸውን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ሃይሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ በአገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የውጭ ባለሀብቶች ከአገር ውስጥ አቻዎቻቸው ጋር በሽርክና (ጆይንት ቬንቸር) ስምምነት እያደረጉ እየሰሩ ይገኛሉ።
ስምምነቱ የአገሪቱን ኢንቨስትመንት በማሳለጥና ዘላቂ እድገት በማስመዝገብ ረገድ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ መኮንን ጠቅሰው፣በተለይ የአገር ውስጥ አምራቾች አቅማቸውን እንዲያዳብሩ የተሻለ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማረጋገጥና ያለባቸውን የገበያ ችግር በማስወገድ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ብለዋል ።
ባለፉት አመታት በርካታ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በሽርክና ሲሰሩ መቆየታቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረው፣እኤአ ከ2014 እስከ 2019 ድረስ ባሉት አምስት አመታት ብቻ 560 የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያውያንና በተለያዩ አገራት ባለሃብቶች ሽርክና (ጆይንት ቬንቸር) መተግበራቸውን አስታውቀዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል 182 የሚሆኑት ማምረትና አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቅሰው፣114 የሚሆኑት ወደ ትግበራ እየተሸጋገሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። 263 የሚሆኑት ደግሞ በቅድመ ትግበራ ላይ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
በተለይ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ከቻይና ውያን አቻዎቻቸው ጋር የመሰረቱት ሽርክና ቁጥሩ ከፍ እንደሚል አስታውቀው፣በ103 ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ እንደሚሰሩም አመልክተዋል።ከአሜሪካ ጋር በ50፣ከህንድ ጋር በ30፣ከኔዘርላንድስ ጋር በ28 ከሳውዲ አረቢያ ጋር በ21፣ ከቱርክ 24 እንዲሁም ከጣሊያን ጋር በ16 ፕሮጀክቶች ላይ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ሽርክን መፍጠራቸውን አብነት በመጥቀስ አመልክተዋል።
እንደ አቶ መኮንን ገለጻ፤ከጠቅላላው የሽርክና ኢንቨስትመንት በማምረቻው ዘርፍ የተሰማሩት ባለሃብቶች ቁጥር የላቀ ነው። በማምረቻ ኢንዱስትሪ 350፣በግብርና 67፣በሪል እስቴት፣ማሽነሪ ዘርፍ 56፣በኮንስትራክሽን 27 እንዲሁም በሆቴልና ሌሎችም ዘርፎች ላይ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች የውጭ አቻዎቻቸው ጋር በጋራ በመስራት ላይ ከሚገኙባቸው ዘርፎች መካከል ይጠቀሳሉ።
መሰል የሽርክና ኢንቨስትመንት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ያስገነዘቡት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ፣ ‹‹የኢትዮጵያ በተለይ በማምረቻ ዘርፍ የተሰማሩት አለም አቀፍ ገበያን ዘልቆ ከመግባት አንፃር ውስንነት አለባቸው፣የሽርክና ኢንቨስትመንቱ መመስረቱ የአገር ውስጥ አምራቾች አቅማቸውን እንዲያዳብሩ የተሻለ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያረጋግጡና የገበያ ችግራቸውን እንዲያቃልሉ ያግዛቸዋል›› ብለዋል
‹‹ኮሚሽኑም ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ሽርክና ለሚመሰርቱ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ልዩ የድጋፍ ማበረታቻ ስርአት ተዘርግቷል››ያሉት አቶ መኮንን፣ በአሁኑ ወቅትም የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ከውጭ ሀገራት ጋር የመስራት ፍላጎት መጨመሩንና የውጭዎቹም ተመሳሳይ ፍላጎት ማሳየታቸውን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2012
ታምራት ተስፋዬ