ታቦታቱ የሚያልፉባቸው አውራ ጎዳናዎች በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ፀድተው፣ መተላላፊያ መንገዶቹና ዋና ዋና አደባባዮች በባንዲራ አሸብርቀው ይታያሉ። ታቦታት ከየአድባራት በካህናት፣ በዲያቆናት እና በምዕመናን ታጅበው በክብር ይወጣሉ።መተላለፊያ ጎዳናዎች በምንጣፍና በቄጠማ ጉዝጓዝ ደምቀዋል።ታቦታቱ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ በምዕመናን ውብ ዝማሬና እልልታ ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህር ይወርዳሉ።
ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ታቦታትን ሊያጅቡ የወጡ ዘማሪያን በተዋበ አልባሳት ደምቀው በስርዓት በተሰደሩ ረድፎች የተዋበ ዘማሬን ያሰማሉ፤ ወጣቶች ተመሳሳይ አልባሳትን በመልበስ በቡድን በቡድን ሆነው ክብረ በዓሉን አድምቀውታል።ጃንሜዳ አሸብርቃለች።ይህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ የአደባባይ ደማቅ ክብረ በዓላት አንዱ የሆነው የከተራ በዓል ልዩ ድባብ ነው፡፡
የከተራ በዓል ትላንት በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በመላው ሀገሪቱ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል። በተለይም በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ቀሳውስት፣ የአድባራትና ገዳማት ተወካዮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ በበዓሉ ላይ ለመገኘት ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የአገር ጎብኚዎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ በበርካታ ካህናት፣ ምዕመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ታጅበው ጃንሜዳ ደርሰዋል።
በየአመቱ ጃንሜዳና በአካባቢው የሚገኙ የ11 ደብራትና ገዳማት ታቦታት የጥምቀት በዓልን በጋራ የሚያከብሩ ሲሆን፥ ትላንት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ ከአድባራትና ገዳማት ጉዞ በመጀመር ምሽት ላይ ጃንሜዳ ደርሰው በክብር ስፍራው አርፈዋል። ታቦታት ወደ ማደሪያቸው ጥምቀተ ባህር ከደረሱ በኋላም አዳራቸውን በዚያው ያደርጉ ሲሆን፥ በካህናትና ዲያቆናት ዝማሬና ሌሎች ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ተከናውኗል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ብፁእ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ጸሎተ ቡራኬ ሰጥተዋል። ከፀሎተ ቡራኬ በኋላ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በየተራ ያሬዳዊ ወረብና መዝሙር አቅርበዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙ ምዕመናን የዘንድሮው የከተራ በዓል ልዩ ድምቀት እንዳለው ይገልፃሉ።ወጣት ሙሉጌታ አየለ የአዲስ አበባ ነዋሪ ነው።ጃንሜዳ በዓሉን ለመታደም መገኘቱን ገልፆ በጥምቀት ዋዜማ የሚከበረው የከተራ በዓል ልዩ ሀሴት እንደፈጠረለት ያስረዳል።
በአገር ባህል ልብስ ተውበው ክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተዋል ወይዘሮ ሮዛ ኩምሳ።“ከተራና ጥምቀት ለኔ ልዩ በዓላት ናቸው፤ ስለዚህ ለኔ ሁሌ ይለይብኛል፤ አሸብርቀን ታቦታተኑ አጅበን በሰላም ስንገናኝ ደስ ይላል” በማለት የበዓሉን ልዩ ድምቀት ይገልፃሉ።
በዓሉ ከእምነት ስረዓቱ ባሻገር የባህል ትሩፋቶች ማሳያና የእርስ በርስ ግንኙነት ማጠንከሪያ መሆኑን ይናገራሉ።የእምነቱ ተከታዮችም በዓሉን ሲያከብሩ በመተጋገዝና የሀገራቸው ሰላም በማስጠበቅ ሊሆን እንደሚገባም ይጠቁማሉ።
ዛሬ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በዘንድሮ አመት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በማይዳሰስ የአለም ቅርስነት መዝገቡ ከሌላ ጊዜ ለየት ያለ ድምቀት ያላበሰው መሆኑ በክበረ በዓሉ ላይ የተገኙ ምዕመናን አስተያየት ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 11/2012
ተገኝ ብሩ