ጎንደር:- በጎንደር ከተማ በጥምቀት በዓል ከ460 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱ የከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የጥምቀት በዓል ላይ ለመታደም ጎንደር ገብተዋል።
የከተማ አስተዳድሩ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በበዓሉ ምክንያት በከተማዋ ከሚገኙ ጎብኝዎች በአገልግሎት ሰጪዎች 450 ሚሊዮን ብርና ለመንግስት ከቲኬት ሽያጭና ሌሎች ገቢዎች 10 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
በከተማው ከጥር 3 እስከ 9 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደው የባህል ሳምንት፤ ሙዚቃና ቴያትርን ጨምሮ በርካታ የኪነጥበብ ስራዎች የቀረቡ ሲሆን የጎንደር አካባቢ ባህላዊ ምግብና መጠጥም ለእይታ ቀርቦ በበርካቶች መጎብኘቱንና በዚህም የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር የራሱ ድርሻ እንዳበረከተ አቶ አስቻለው ተናግረዋል።
በዘንድሮው የጥምቀት በዓል ቀደምት ነገስታት ለህዝባቸው ይከውኑት የነበረውን የግብር ማብላት ስነስርዓት ለማስታወስና የጎብኝውን ቁጥር ለማሳደግ በአፄ ፋሲል ቤተመንግስት ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች የንጉስ እራት የተዘጋጀ ሲሆን፤ የነገስታትን ክዋኔ የሚያሳይ ህይወት በአብያተ መንግስት የሚል ትወናም ዛሬ በቦታው ለእይታ እንደሚቀርብ አቶ አስቻለው ተናግረዋል።
በከተማዋ ቱሪስቶች ደረጃውን የጠበቀና የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የተሰራ ሲሆን፤ የውጪ ጎብኝዎች አማካይ የቆይታ ጊዜ ከአንድ ቀን ወደሁለት ቀን፣ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ከሁለት ወደ ሶስት ቀን ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ሀላፊው ተናግረዋል።
በያዝነው ጥር ወር ብቻ ከ30 ሺህ በላይ የውጪ ሀገር ጎብኝዎች የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ ጎንደርን እንደሚጎበኙ የተናገሩት ሀላፊው በኮንፈረንስ ቱሪዝም፤ በሀይማኖት፣ በስፖርት እና ሌሎች ዝግጅቶች የሚታደሙ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችም ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
በጎንደር እየተከበረ ባለው የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የዩኔስኮ ተወካዮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው ኤርትራውያን እንግዶች፣ ጎብኝዎች እና የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል። በክብረ በዓሉ ላይ ከ 2 ሚሊዮን በላይ እንግዶችና ምዕመናን በመታደም ላይ ሲሆን ሁነቱን ለመዘገብ ከአገር ውስጥና ከውጪ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ከ90በ ላይ ጋዜጠኞች በቦታው መገኘታቸው ተጠቁሟል፡፡
የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በማይዳሰስ የአለም ቅርስነት ከተመዘገበ በኋላ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ በመከበር ላይ ሲሆን ይህም ለበዓሉ የተለየ ድባብ አላብሶታል፡፡
ዘንድሮ በልዩ ድምቀት እየተከበረ ባለው የጥምቀት በዓል ላይ ለመታደም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ፣ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ጎንደር መግባታቸው ተገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 11/2012
ድልነሳ ምንውየለት