አዲስ አበባ፡- በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ የነበረው ድርድር የኢትዮጵያን መብት የሚያስጠብቅ እና ግብፅ ላቀረበቻቸው ያልተገቡ ጥያቄዎች ትክክለኛው መልስ የተሰጠበት እንደነበር የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናግረዋል።
የድርድሩን ሂደትና ግድቡ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ማብራሪያ አቅርበዋል።
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ እና ለተወሰኑ የካቢኔ አባላት የቴክኒክ ኮሚቴው ያካሄደውን ድርድር አስመልክቶ ትናንት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በድርድሩ ግብፅ ለምታቀርባቸው ያልተገቡ ጥያቄዎች አስፈላጊው ምላሽ በመስጠት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷ እንዲረጋገጥ ተሰርቷል።
ድርድሩ ግብፅ ከህዳሴው ግድብ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ውሃ በየዓመቱ ይልቀቅ ከሚለው ሃሳብ በተጨማሪ የሙሊት ጊዜውን በሚመለከት ሊሆኑ የማይችሉ ሃሳቦችን አቅርባ እንደነበር አመልክተው፤ በኢትዮጵያ በኩል ግን ለሁሉም ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን በመሰንዘር ውሃ የሚያዘው በኢትዮጵያ ወንዞች የሚሞሉበትን ጊዜያት ማለትም ሃምሌ፣ ነሐሴና መስከረምን በመጠቀም ለመሙላት የታቀደ መሆኑን ተናግረዋል።
በእነዚህ ጊዜያት የህዳሴውን ግድብ መሙላት ለግብፅም ሆነ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ከጎርፍ ከመታደግ ባሻገር በቀጣይ መጠባበቂያ ውሃ እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ድርድሮች ሲካሄዱ እንደነበር ያብራሩት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፤ በአራቱም ድርድሮች በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የነበረውን ብዥታ ለማጥራት መጥቀሙን አብራርተዋል።
የግድቡ ሙሊት ሲካሄድ ወደ ታችኛው ተፋሰስ አገራት ውሃ የሚወርድ ያልመሰላቸው እንደነበሩ በመጠቆም፤ በኢትዮጵያ በኩል የአገርን ጥቅም ከማስጠበቅ ውጪ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት የመጉዳት ዕቅድ አለመኖሩን ማስረዳት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በየዓመቱ ውሃውን ከመሙላት ባሻገር ድርቅ ሲያጋጥም የተሞላ የመጠባበቂያ ውሃ ለታችኞቹ ተፋሰስ አገራት የሚለቀቅ መሆኑን ተናግረዋል።ከዚህ አንፃር ግድቡ ለታችኞቹ ተፋሰስ አገራት መጠባበቂያ ውሃ እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
ድርድሩ ወደ ፊት በቴክኒካል ኮሚቴው የተደረሱባቸው ስምምነቶች የህግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው ከየአገራቱ ሶስት ሶስት የህግ ባለሙያዎች ተገናኝተው የሚያዘጋጁት መሆኑን ጠቁመው፤ በጉዳዩ ላይ መመሪያ እንደሚዘጋጅ እና መመሪያውም በየአምስት አመቱ እንደሚከለስ ጠቁመዋል።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድቡን የግንባታ ሂደት አስመልክቶም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ የግድቡ ግንባታ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን እና ከ70 በመቶ በላይ መገንባቱን እንዲሁም ወደ ኋላ የቀሩ ስራዎችን በማፋጠን እና ጥራታቸውን የጠበቁ ብረቶችን ከውጪ በማስገባት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 11/2012
ምህረት ሞገስ