አዲስ አበባ:- የደብረብርሃን ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በመሳብ በአምስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ10 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ማስመዝገብ መቻሉ ተጠቆመ።
የደብረብርሃን ከተማ ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በአሁኑ ወቅት መዋለ ንዋያቸውን በከተማዋ በማፍሰስ ትላልቅ ፋብሪካዎችን እየገነቡ ይገኛሉ።
በያዝነው ዓመት አምስት ወር ብቻ 83 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ከተማዋ በመምጣት ለማልማት ተዘጋጅተዋል። ከእነዚህም መካከል 40 ለሚሆኑ ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት ዝግጁ የሆነ መሬት መሰጠቱን ከንቲባው ገልጸዋል።
በገቢ ደረጃ በአምስት ወራት ውስጥ ከእነዚሁ ባለሀብቶች ከ10 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ተገኝቷል። ከዚህም በላይ በከተማዋ ሀብት እየፈጠሩ ያሉት ባለሀብቶች ከ20 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ይገመታል በማለት አቶ ደስታ ተናግረዋል።
በደብረብርሃን ከተማ አሁን ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ፈጣን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ማንኛውም ባለሀብት ላልማ ብሎ ወደ ከተማዋ ሲመጣ ያለምንም ልዩነት እና ቢሮክራሲ ማንም ይሁን ማን ይስተናገዳል ያሉት አቶ ደስታ፤ ምክንያቱም ደብረብርሃን ከተማ የሁሉም ዜጎች ከተማ መሆኗን በማመን የሚሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ትላልቅ ፋብሪካዎችን ለመገንባትና በዚያው ልክ ደግሞ ሰፊ የሥራ ዕድል በከተማዋ ለመፍጠር እየተሰራ ከመሆኑም በላይ በአሁኑ ወቅት 2ሺ 500 ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት መዘጋጀቱን አሳውቀዋል።
«የደብረብርሃን ከተማ ፍፁም ሰላማዊና የተረጋጋች ከተማ ናት። ወጣቱ ሰርቼ ልለወጥ የሚል ነው። ኅብረተሰቡ ኢንዱስትሪ መጣ ሲባል እሰይ ከተማችን ሊለወጥ ነው እኛም አብረን ልንለወጥ ልናድግ ነው የሚል አስተሳሰብ አለው።» በማለት የተናገሩት ከንቲባው፤ ደብረብርሃን ላይ ኢንቨስት ለሚያደርግ ባለሀብት ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚሰጠው ገልጸዋል።ጨምረውም ወደ ከተማዋ የሚመጡ ሰፊ ቁጥር ያላቸው የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከተማዋ በሯን ከፍታ እየተቀበለች መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 11/2012
ፍሬህይወት አወቀ