አዲስ አበባ፡- ባለፈው በጀት ዓመት በአዲስ አበባና አካባቢው በ167 የርቀት ማስተባበሪያ ተቋማት ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በህገወጥ የርቀት ትምህርት ሥራ ላይ የተሰማሩ 24 ተቋማት እንዲዘጉ መደረጉን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ገለፀ።
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የእውቅና አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ አብይ ዳባይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ኤጀንሲው አዲስ አበባና በአካባቢው በ2011 ዓ.ም በ167 የርቀት ማስተባበሪያ ተቋማት ላይ ዳሰሳዊ ጥናት አድርጎ ነበር።ከዚህ ውስጥ 46 ተቋማት የተለያዩ ህገወጥ ድርጊት ውስጥ ተሳትፈው ተገኝተዋል።ከ46 ተቋማት ውስጥ 24 ተቋማት ላይ ማጣራት ተደርጎ እስከ መዝጋት የደረሰ እርምጃ ተወስዶባቸዋል።
ኤጀንሲው እውቅና የሚሰጠው የሞጁል፣ የፈተና ዝግጅት፣ የካሬኩለም ቀረፃ እና የምዘና ስርዓት በአግባቡ ለሚከናወንበት ማእከል እንደሆነ ገልፀዋል።አብዛኛዎቹ ተቋማት በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ ማዕከል ያላቸው ሲሆን፤ ይህን ተከትሎ ለተማሪዎች ተደራሽ ለመሆን ቅርንጫፍ ማዕከላትን በመክፈት ለተማሪዎች በቅርበት አገልግሎት እንደሚሰጡ ጠቅሰዋል።ከዚህ ጋር ተያይዞ አብዛኛዎቹ ተቋማት የኤጀንሲውን ፈቃድ ሳያገኙ በወረዳና በቀሌዎች ላይ የማስተባበሪያ ማዕከላትን ከፍተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የርቀት ተማሪዎች በዓመት ሁለት ጊዜ የገፅ ለገፅ ገለፃ ማግኘት እንዳለባቸው በመመሪያ መቀመጡን በመጥቀስ፤ ብቁ መምህራን በሌሉባቸው አካባቢዎች ቅርንጫፍ ከፍተው በመስራታቸው ምክንያት ተማሪዎቹ በቂ እውቀት እያገኙ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ፈተና እና አሳይንመንት ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ የሚሰጥ በመሆኑ መመዘኛዎቹን ተማሪዎች ሳይሆኑ የተማሪዎቹ ዘመዶች፣ ቤተሰቦች እና ሌሎች ከትምህርቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች የሚሰሩበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀዋል።በተለይ አሳይንመንት ሲሰጥ እራሳቸው ሰርተው ብቃታቸውን መለካት ሲገባቸው በሌሎች ሰዎች ማሰራት በስፋት እንደሚስተዋልም አብራርተዋል።
አቶ አብይ እንደሚናገሩት፤ ለከፍተኛ ትምህርት ብቁ ያልሆኑ ተማሪዎች መዝግቦ ማስተማር በተለይ ከአስረኛ ክፍል ያልጨረሱ፣ ደረጃ አራት ያልደረሱ እና የብቃት ማረጋገጫ የሌላቸውን ተማሪዎች መቀበል እንዲሁም በአጠቃላይ አገሪቱ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ መስፈር አለማክበር ከተስተዋሉ ክፍተቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
ተማሪዎች በአግባቡ ለትምህርቱ የሚያስልጋቸውን የጊዜ ቆይታ ሳያሳልፉ የትምህርት ማስረጃ መስጠት ይታያል ካሉ በኋላ፤ ይህ ጉዳይ ዲግሪ መሸጥንም የሚያካትት መሆኑን አብራርተዋል።አንዳንድ ተቋማት ተማሪው ከዚህ በፊት እንደተመዘገበ በማድረግ ዶክመንት አዘጋጅተው ትምህርቱን ላልተከታተለ ሰው ማስረጃ የሚሰጡበት ሁኔታ መኖሩንም ነው የተናገሩት።
አጠቃላይ ከተሰሩ ዳሰሳዎች በመነሳት አዲስ ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱን የጠቀሱት አቶ አብይ፤ ኤጀንሲው በየክልሉ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አለመክፈቱና በተቋማት ልክ ኤጀንሲው አለማደጉ ችግሮች እንዲባባሱ ማድረጉ በዳሰሳ ጥናቱ መታየቱን ተናግረዋል።ባህላዊ የቁጥጥር ስርዓትን በመተው በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ለመፍጠር በቀጣይ መታሰቡን አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 11/2012
መርድ ክፍሉ